አሸባሪው ህወሃት በህዝብ ላይ የፈፀመው የጭካኔ ተግባር ዳግም እንዳይከሰት ትውልድ ሊማርበት ይገባል

57

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) አሸባሪው ህወሃት በህዝብ ላይ የፈፀመው የጭካኔ ተግባርና ቁሳዊ ውድመት በኢትዮጵያ ዳግም እንዳይከሰት የትውልድ መማሪያ ሊሆን ይገባል።

"ሥለ ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያዘጋጀው የፎቶ ግራፍ አውደ ርዕይ ለጎብኝዎች ክፍት ሆኗል።    

የፎቶ አውደ ርዕዩ አሸባሪውን ህወሃት በመፋለም መከላከያ ሰራዊቱን ጨምሮ አጠቃላይ ህዝቡ ያደረገውን ተጋድሎ የሚያስቃኝ ሲሆን አሸባሪው ቡድን ወረራ ፈጽሞባቸው በነበሩ አካባቢዎች በነዋሪዎችና በማህበረሰብ አገልግሎት ተቋማት ላይ የፈፀማቸውን በደልና ግፍ ያመላክታል።

ከአውደ ርዕዩ ጎን ለጎንም በመክፈቻ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተካፈሉ እንግዶች የፓናል ውይይት አካሂደዋል።

በውይይቱ ላይ ሀሳባቸውን የሰጡት የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሙአዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ አሸባሪው ህወሃት በህዝብ ላይ የፈፀመው የጭካኔ ተግባርና ቁሳዊ ውድመት በኢትዮጵያ ዳግም እንዳይከሰት የትውልድ መማሪያ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

"ለዚህ ደግሞ አሸባሪው በህዝብ ላይ የፈጸማቸውን አሰቃቂ ተግባራትና በመሰነድ ትውልዱ እንዲያውቀው ማድረግ ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

አሸባሪው ህወሃት በሲቪል፣ በሞራል፣ በባህልና በሀይማኖት የማይገዛ ቡድን መሆኑን በአውደ ርዕዩ የቀረቡ የፎቶ ግራፍ ማስረጃዎች እንደሚያመላክቱም ገልጸዋል።

ለሃይማኖት እንደማይገዛ ያወደማቸው የእምነት ተቋማት ምስክር እንደሆኑ ተናግረዋል።

በአሸባሪው ህወሃት የተፈጸሙ ድርጊቶች ለትውልድ ማስተማሪያ ሲሆኑ አንዳንድ የሀሳቡ ደጋፊዎችም እንዳይነሱ ያደርጋል ብለዋል።

ድርጊቱ ለአንድነት ሲባል ይቅር ሊባል ቢችልም እንዳይደገም፣ ሌላው እንዳይከተለው፣ ጥፋቱን እንደአረአያ የሚቆጥር ትውልድ እንዳይነሳ ለማድረግ ሲባል ትውልድ እንዲማርበት ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የእስልምና ሃይማኖት መምህሩ ዑስታዝ አቡበከር አህመድ የአሸባሪው ክፋት የሚመነጨው ከተፈጥሮአዊ ባህሪው መሆኑን ገልጸው፤ ቡድኑ ህጻናትን መድፈሩ፣ በችግር ጊዜ መጠጊያና መጠለያ የሆኑትን የእምነት ተቋማት ማውደሙ ሞራል አልባነቱን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አብራርተዋል።   

የአሸባሪው ህወሃት የጥፋት እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያዊያን ይበልጥ አንድ መሆንና ጠላትን በጋራ መመከት አስችሏቸዋል ብለዋል።     

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ዶክተር አጋራደች ጀማነህ በአሸባሪው ህወሃት የጥፋት ድርጊት ሰለባ የሆኑ ዜጎች ታሪክ ገና ብዙ ሊነገር ይገባዋል ብለዋል።

የፎቶ አውደ ርዕዩ ታሪክን ሰንዶ ለማቆየት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ ጥናትና ምርምር ማድረግ ለሚፈልጉ አካላት ግብዓት ይሆናል ነው ያሉት።

በአውደ ርዕዩ ላይ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶክተር ለገሰ ቱሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክረቴሪያት የውጭ ቋንቋዎችና ዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም