የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ በግል የትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ አሳሰበ

125

አዲስ  አበባ፤ ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ)  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ በግል የትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች እንዲስተካከሉ አሳሰበ።

የምክር ቤቱ የመንግስት አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዲስ አበባ የሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶችን አስመልክቶ ዋና ኦዲተር ላቀረበው የክዋኔ ኦዲት ትምህርት ሚኒስቴር  የሰጠውን ምላሽ አድምጧል።

በ2012 እና በ2013 ዓ.ም በህዝብ የውይይት መድረክ ተነስተው ምላሽ ያሻቸዋል ያላቸውን ጉዳዮችም ቋሚ ኮሚቴው ጠቅሷል።

ከእነዚህ መካከል በግል የትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ላይ የሚስተዋሉ ክፍተቶች መሆናቸውን በማስታወስ በአፋጣኝ ሊታረሙ እንደሚገባ አሳስቧል።

በ1987 ዓ.ም የወጣው የተቋማቱ የፈቃድ አሰጣጥና የቁጥጥር ደንብ ዘመኑን ያልዋጀ በመሆኑ ማሻሻያ እንዲደረግበት ተነስቶ እስካሁን አለመተግበሩን ቋሚ ኮሚቴው ጠቅሷል።

በአንዳንድ የማህበረሰብና አለም አቀፍ ትምህርት ቤቶች ላይ የትምህርት ስርአቱ ከአገሪቱ ፖሊሲ፣ አሰራርና ባህል ያፈነገጠ መሆኑ እየተስተዋለ የተወሰደ እርምጃ የለም ያለው ቋሚ ኮሚቴው ለጉዳዩ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል።

በተቋማቱ የምክርና ድጋፍ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች አለመኖር፣ ለመምህራን የብቃት ምዘና አለመስጠት ላይ ባለፉት ስድስት ወራት የተወሰዱ የማሻሻያ ስራዎች እንዲብራሩም ተጠይቋል።

የቋሚ ኮሚቴውን ጥያቄ ተከትሎ ሚኒስቴሩ በሰጠው ምላሽ የግል ትምህርት ቤቶችን ችግር ለመፍታት የዲፕሎማሲና የህግ ክፍተቶች ማነቆ ሆነውብኛል ብሏል።

ላለፉት 27 ዓመታት ሲያገለግል የቆየው የግል ትምህርት ተቋማት ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር ደንብን ለማሻሻል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለሚንስትሮች ምክር ቤት መቅረቡም ተጠቅሷል።

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የትምህርት ጥራትን ለማስጠበቅ በአገሪቱ በትምህርት ዘርፍ ላይ የወጡ መመሪያዎችና ደንቦች ላይ ሰፊ ማሻሻያ  እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል።

በተደረገው ጥናት 90 በመቶ የሚሆኑ የትምህርት ተቋማት ለትምህርት የተሰጠውን ደረጃ አያሟሉም ያሉት ሚኒስትሩ ለዚህም ሰፊ ስራ ይጠይቀናል ብለዋል።

ምክር ቤት የመንግስት አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ክርስቲያን ታደለ፤ ሚኒስቴሩ የህዝብ ጥያቄዎችና በኦዲት ግኝቱ ላይ አፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱና የመመሪያ ማሻሻያዎችን በፍጥነት አለማከናወኑ በግልፅ የታየ ድክመት መሆኑን ጠቅሰዋል።

በበጎ አድራጎት ስም ተመስርተው ወደ ንግድ ትምህርት ተቋማትነት የተቀየሩና የአገሪቱን ባህልና ህግ የሚጻረሩ የግል የትምህርት ተቋማት ላይ አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ አለመወሰዱም እንዲሁ።

በመሆኑም ደንቦችና ህጎች አሁን ካለው አስተሳሳብ ጋር ተቃኝተው እንዲተገበሩ እንዲሁም በኦዲት ግኝት ማሻሻያ ላይ የታየው መዘናጋት በአፋጣኝ እንዲስተካከል አሳስበዋል።

በሚኒስቴሩ በኩል አፋጣኝ መፍትሄ የሚሹና የሚስተካከሉ ጉዳዮችን ጠቅሰው የሚወሰዱ የመፍትሄ እርምጃዎች በቀጣይ አስራአምስት ቀናት ለቋሚ ኮሚቴውና ለሚመለከታቸው አካላት እንዲያቀርብ አሳስበዋል።

ሚኒስቴሩ ለሚያከናውናቸው የመፍትሄ እርምጃዎችና የማሻሻያ ስራዎች ቋሚ ኮሚቴው ለማገዝ ዝግጁ ነው ሲሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም