ኢንስቲትዩቱ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በችግር ውስጥ ለሚገኙ ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አደረገ

74

ታህሳስ 25/2014 (ኢዜአ)  የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ድጋፉንም የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር አለበል ደሴ በወልዲያ ከተማ በመገኘት ለዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋሁን ብታብል አስረክበዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ በዚህን ወቅት አሸባሪ ቡድኑ በወረራ ይዟቸው በቆየባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረሱን ገልጸዋል።

በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መደገፍና የወደሙ ተቋማትንም መልሶ መቋቋም ደግሞ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የፓሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት በሰሜን ወሎ ዞን ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች የሚውል የምግብ ነክ ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸው፤ ድጋፉ በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋሁን ብታብል በበኩላቸው ኢንስቲትዩቱ ላደረገው ድጋፍ  ምስጋና አቅርበው፤ ሌሎች አካላትም በተመሳሳይ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የፓሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም