ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ግብር በአግባቡ እንዲሰበሰብ ባለድርሻዎች ሀላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

50

ባህር ዳር ታህሳስ 25/2014- (ኢዜአ) ኢኮኖሚው የሚያመነጨው ግብር በአግባቡ ተሰብስቦ ለልማት እንዲውል ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አስገነዘቡ ።

በአማራ ክልል የገቢ ፍኖተ ካርታ ጥናት የምክክር መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሂዷል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ዶክተር ይልቃል ከፋለ በወቅቱ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት ከክልሉ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ዝቅተኛ ነው።

የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ፣ የኢንቨስትመንት ዘርፉን ለማስፋፋትና ህዝብን የሚጠቅሙ መሰረተ ልማቶችን ለመገንባት የግብር ገቢን ማሳደግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዶክተር ይልቃል እንዳሉት ከክልሉ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ለሠራተኛ ደመወዝና ለተቋማት የሥራ ማስኬጃ ከመዋል የሚያልፍ አይደለም።

"የክልሉን ገቢ በማሳደግ ልማትን ለማፋጠንና ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ሁሉም ባለድርሻ አካል ኢኮኖሚው በሚያመነጨው ልክ ግብር እንዲሰበሰብ ሃላፊነቱን መወጣት ይኖርበታል" ብለዋል።

ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ እንዲከፍል ምሁራን በጥናት ላይ የተረጋገጠ አቅጣጫ ማሳየት እንዳለባቸው አመልክተዋል።

ገቢ በመሰብሰብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች ግብርን በወቅቱ መሰብሰብ፤ የንግዱ ማህበረሰብም የሚጣልበትን ግብር በሃላፊነት መክፈል እንዳለበት ገልፀዋል።

በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ስርአቱ አለመዳበር ለገቢው ዝቅተኛ መሆኑን አይነተኛ ምክንያት መሆኑን ጠቁመዋል ።

"አሁን ያለው የግብር አሰባሰብ ስርአት ለውጥ ያስፈልገዋል" ያሉት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ ለእዚህም በዘርፉ ጥናት መካሄዱንና በቀጣይ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት ተደርጎበት ተግባራዊ እንደሚሆን አመላክተዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ፀጋ ጥበቡ በበኩላቸው የገቢ አሰባሰብ ስርአቱን ለማዘመንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ በምሁራን ጥናት መካሄዱን ገልጸዋል።

ግብር በታቀደው ልክ የሚሰበሰበው በቅንጅት መስራት ሲቻል እንደሆነ ጠቁመው፣ ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

የዘርፉን አሰራር ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ያለምንም ክፍያ ጥናት ከማድረግ ጀምሮ ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የአምስት ዓመት የገቢ ፍኖተ ካርታ ጥናት መካሄዱን ጠቁመው ጥናቱ በውይይት ዳብሮ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስታውቀዋል።

"በገቢ አሰባሰብ ስርአቱ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ ቴክኖሎጂን መጠቀም ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ በገቢ ፍኖተ ካርታ ጥናት ተሳታፊና የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስና አካውንቲንግ መምህር ዶክተር ለጤናህ እጅጉ ናቸው።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ደካማ መሆኑን ጠቁመው "የግብር ከፋዩን ህብረተሰብ መረጃ በግልጽና በማያሻማ ሁኔታ ማደራጀት ያስፈልጋል" ብለዋል።

ቢሮው ከሌሎች ተቋማት ጋር ስራዎችን በትብብርና በቅንጅት መስራት እንደሚጠበቅበትም አመልክተዋል።

"አንዳንድ ባለሀብቶች በስራቸው ልክ ግብር መክፈል አይፈልጉም፣ ይሄ የሞራል መላሸቅ ነው'' ያሉት ደግሞ ባለሃብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ናቸው።

ባለሃብት ከራሱ አልፎ ለሀገሩ የሚተርፍ ሥራ የሚሰራ መሆን እንዳለበት ገልጸው "ይህንን ያልተረዳና የሚጠበቅበትን ግብር የማይከፍል ባለሃብት የአገርና የህዝብ ፍቅር የለውም " ሲሉ በአጽኖት ተናግረዋል።

በተለይም አሁን አገር ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ የሚጠበቅበትን ግብር በማይከፍል ባለሃብት ላይ ተገቢው እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ የሚከፍሉ ነጋዴዎችን መሸለምና ማበረታታት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ተናግረዋል።

ባለሀብቱ እንዳሉት በአመራሩ በኩል ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ፈልጎ የማግኘት ከፍተት አለ።

"ግብሩን በአግባቡ የሚከፍል ላይ ብቻ አተኩሮ የመስራት አዝማሚያ ስለሚስተዋል መስተካከል አለበት" ብለዋል

አመራሩ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ የመረጃ አያያዝ ስርአትን በመዘርጋት ህገ-ወጥ ነጋዴዎችን ተከታትሎ በመያዝ በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚገባ አቶ በላይነህ አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ ላይ የክልልና የፌዴራል መንግስት አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም