አሸባሪው የህወሃት ቡድን ባደረሰው ውድመት ተስፋ ሳንቆርጥ የከተማችንን እንቅስቃሴ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንሰራለን

72

ደሴ ፤ ታህሳስ 25/2014 (ኢዜአ) አሸባሪው የህወሃት ቡድን በከተማችን ውድመት ቢያደርስም ተስፋ ሳንቆርጥ አሁን ባገኘነው የሰላም አየር የከተማችንን እንቅስቃሴ ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ እንሰራለን ሲሉ የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

ነዋሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኮምቦልቻ ከተማ ተቋማትና ድርጅቶች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸው ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ያስችላል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ብርሃን ጌታሁን በሰጡት አስተያየት፤ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የኢንዱስትሪ ከተማ የሆነችውን ኮምቦልቻን መዝረፉና ያልቻለውን ደግሞ ማውደሙ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር የጥፋት ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።

ቡድኑ በመከላከያ ሠራዊትና በሌሎች የጸጥታ ሀይሎች በተወሰደበት እርምጃ ከከተማዋ ተገፍቶ በመውጣቱ አሁን ላይ በከተማዋ ሰላምና መረጋጋት ታይቷል ነው ያሉት።

ወራሪውና አሸባሪው ህወሓት ከተማዋን ወሮ በቆየባቸው ጊዜያት ከፍተኛ ውድመት ቢያደርስም በእዚህ ተስፋ ሳትቆርጡ አሁን በተገኘው  ሰላም የከተማዋን እንቅስቃሴ ለማነቃቃት በቁጭት መነሳሳታቸውን ገልጸዋል።

መንግስት የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ባደረገው ጥረት ባንኮች፣ የጤና ተቋማት፣ የንግድ ድርጅቶችና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ሥራ መጀመራቸውንም አቶ ብርሃን ተናግረዋል።

መንግስት የጀመረውን መልሶ የማልማትና የማቋቋም እንቅስቃሴ ለከተማዋ የኢኮኖሚ መነቃቃት አስተዋጾ ስለሚኖረው የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ወይዘሮ ዘቢባ መሃመድ በበኩላቸው፤ አሸባሪው ቡድን በከተማቸው በቆየባቸው ጊዜያት ንጹሃንን በመግደል፣ ሃብትና ንብረት በመዝረፍ እንዲሁም ያልቻለውን በማውደም  የህብረተሰቡን ህይወት ማመሰቃቀሉን አውስተዋል።

"የሽብር ቡድኑ በኢንዱስትሪና በኢንቨስትመንት በፍጥነት እያደገች የነበረችውን ኮምቦልቻን በመዝረፍና በማውደሙ የከተማዋ እድገቷ ወደኋላ እንዲመለስ ማድረጉ ከህሊና የማይጠፋ ጥቁር ጠባሳ ነው" ብለዋል።

አሸባሪው በከተማችን ከፍተኛ ውድመት ቢያደርስም ተስፋ እንደማይቆርጡ ገልጸው፤ አሁን ባተገኘው  የሰላም አየር በየሥራ ዘርፉ የከተማዋን እንቅስቃሴ ቀድሞ ወደ ነበረበት ለመመለስ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት የሚያስችሉ ተቋማትና ድርጅቶች ወደሥራ መግባታቸው የከተማዋን እንቅስቃሴ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ወሳኝ መሆኑንም ወይዘሮ ዘቢባ አመልክተዋል።

ተፈናቀለው የነበሩ የከተማዋ ነዋሪዎች መመለሳቸው ተባብረውና ተረዳድተው የከተማዋን  የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አጠናክሮ ለማስቀጠል አጋዥ መሆኑንም አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይ አቶ አረቡ መሃመድ፤  ከተማዋን ቀድሞ ወደ ነበረችበት እንቅስቃሴ ለመመለስ እየተሰራ በተወሰነ ደረጃ ለውጥ እየመጣ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይ የገበያ ማዕከላት፣ የትራንስፖርት፣ የመብራትና የኤሌክትሪክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ህብረተሰቡ በአሸባሪው ህወሓት በተፈጸመበት ግፍ ከደረሰበት የስነ ልቦና ጫና ወጥቶ ፊቱን ወደ ልማት እንዲዞር ማስቻሉን አመልክተዋል።

እንደ አቶ አረቡ ገለጻ፤  ኮምቦልቻ ከተማና አካባቢው ነጻ ከወጣ ማግስት ጀምሮ ከህብረተሰቡና  ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር የተደረገው ውይይት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ በማቃለል  ወደ ሥራ ለመግባት እያገዘ ነው።

"በአሸባሪው የህወሓት ቡድን በከተማዋና ነዋሪዎቿ ላይ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ ቢሆንም በእልህ፣ በቁጭትና በቅንጅት በመስራት የኢንዱስትሪ ከተማነቷን አስጠብቃ እንድትዘልቅ እናደርጋታለን" ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም