ከ109 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ዙር የሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጀመረ

70

ታህሳስ 25/2014/ኢዜአ/ በአዲስ አበባ ከ109 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሁለተኛ ዙር የሴፍቲኔትና የምግብ ዋስትና ፕሮግራም ተጀመረ።

በመርሃ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፤ ከድህነት ወለል በታች ያሉ በርካታ ዜጎችን ህይወት በማሻሻል በዘላቂነት ለማቋቋም የተቀየሱት የድህነት ቅነሳ ፕሮግራሞች ውጤታማ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የከተማዋን ዘርፈ ብዙ ችግሮች በመፍታት ከድህነት ወለል በታች የሆኑ ዜጎች በተለያዩ ሞያዎች ሰልጥነው ወደ ስራ በመግባት ከእለት ገቢያቸው አልፈው ጥሪት ማፍራታቸውን ገልጸዋል፡፡

በልማታዊ ሴፍቲኔት የመጀመሪያው ምእራፍ ሁለተኛው ዙር የተደራጁና ከድህነት ወለል በታች የነበሩ 49 ሺህ 204 ዜጎች ወደ ዘላቂ አድገት መሸጋገራቸውን በማሳያ አንስተዋል፡፡

ይህን ፕሮግራም በማስቀጠልም በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ምእራፍ የከተማ ምርታማነት ሴፍቲኔት የስራ ፕሮጀክት 109 ሺ 918 ሰዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮግራም መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በዚህ መርሃ ግብር ተጠቃሚዎችም በአረንጓዴ ልማት፣ በአካባቢ ጥበቃ፣ በአነስተኛ መሰረተልማት ግንባታ፣ በደረቅ ቆሻሻ አወጋገድና አካባቢን የማስዋብ ስራ እንደሚሰማሩ ጠቁመዋል፡፡

በልማታዊ ሴፍቲኔት ተደራጅተው ሀብት አፍርተው ከተመረቁት መካከል አቶ አሚን ከድር፤ የቆሸሹ አካባቢዎችን አፅድተው አትክልት በማልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ይናገራሉ።

በስራ ቆይታዬም በትጋት ከተሰራ መለወጥ እንደሚቻል በአግባቡ ተገንዝቤያለሁ ብለዋል።

በሴፍቲኔት መርሀ ግብሩ ታትረው በመስራት ራስንና ቤተሰብን ማስተዳደር ተምሬበታለሁ የሚሉት ደግሞ ወይዘሮ ትግስት ብርሀኑ ናቸው፡፡

መንግስት ባመቻቸላቸው በቆዳ ስራ ስልጠና ወደ ስራ በመግባት ከድህነት ወጥተው ወደ መካከለኛ ገቢ መቀላቀላቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ታቅፈው ሲሰሩ ቆይተው ወደ ዘላቂ የኑሮ እድገት የተሸጋገሩ 49 ሺህ 204 ዜጎችም ተመርቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም