የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባኤ ተመሰረተ

84
ባህር ዳር ነሀሴ 21/2010 የአማራ ክልል ምሁራን መማክርት ጉባኤ ዛሬ በባህርዳር ከተማ ተመሰረተ። የመማክርት ጉባኤው የተመሰረተው ከተለያዩ የዓለም አገራትና ከአገር ውስጥ የተወጣጡ ምሁራን በባህርዳር ከተማ ላለፉት ሶስት ቀናት ያካሄዱት የምክክር መድረክ ማጠናቀቂያ ላይ ነው። ለመማክርት ጉባኤው 105 የጠቅላላ ጉባኤና 15 የቦርድ አባላት ተሰይመዋል። የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በምስረታው ላይ እንዳሉት የአማራ ክልልን ህዝብ ልማት፣ ሰላምና እድገት ለማረጋገጥ ምሁራንና ባለሃብቱን በማስተባበር ማሳተፍ አስፈላጊ  ነው። ''የተመሰረተው የመማክርት ጉባኤም ፍትህና ነጻነት እንዲነግስ እንዲሁም ዴሞክራሲያዊ ልዕልና እንዲጎለብት መሳሪያ ሆኖ ያገለግላል የሚል እምነት አለኝ'' ብለዋል። ጉባኤው የአማራን ባህልና እሴት በእውቀትና ክህሎት ታግዞ እንዲገነባ ለማድረግና ለአገራዊ አንድነት እውን መሆን የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል። ተቋሙ በሚሰራው መልካም ስራ በታሪክ ተጠቃሽ ሆኖ እንዲዘልቅ የክልሉ መንግስት ለህዝቡ በማስተዋወቅና ለሌሎች ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ ተናግረዋል። የመማክርት ጉባኤው ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት ዶክተር ገበያው ጥሩነህ በበኩላቸው የጉባኤው መመስረት በአገሪቱ ለተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ትልቅ አቅም ይፈጥራል፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ምሁራንን በማሳተፍም ለክልሉ ህዝቦችም ሆነ ለአገር አቀፍ የሚበጅ ተግባር ለማከናወን ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥርም ተናግረዋል፡፡ የጉባኤው አባላትም ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅን በመጠቀም በየትኛውም የዓለም አገራት ሆነው ለክልሉ ልማትና ሰላም አስተዋጽኦ የሚያደርጉበት ሁኔታ እንደሚመቻች ገልፀዋል፡፡ ዛሬ በተካሄደው የምሁራን መማክርት ጉባኤ ምስረታ የተሰየሙት የጠቅላላ ጉባኤና የቦርድ አባላት ለክልሉ ህዝብ ጥቅም ለመስራት ቃል ገብተዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም