ፕሮጀክቶችን ያለምንም ተጨማሪ በጀት ማጠናቀቅ የመንግስትን የአፈፃፀም ብቃት ያሳያል

83

ታህሳስ 24/2014/ኢዜአ/ ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ፕሮጀክቶችን በታሰበው ጊዜ ያለምንም ተጨማሪ በጀት ማጠናቀቅ መቻል የመንግስትን የአፈፃፀም ብቃት የሚያሳይ መሆኑ ተገለፀ።


ከለውጡ ወዲህ ባሉ ሶስት ዓመታት የተገነቡት የመስቀል አደባባይ፣ የአንድነትና የእንጦጦ ፓርክ፣ የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክትን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቅቀዋል።

ትላንት ለምረቃ የበቃው አብርሆት ቤተ መጻሕፍት ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ የማጠናቀቅ ሌላው ማሳያ ነው።

በ18 ወራት ጊዜ ውስጥ የተገነባው ግዙፉ ቤተ መፃሕፍት 1 ነጥብ 15 ቢሊዮን ብር የፈጀ እና በታለመው ጊዜ ተገንብቶ የተጠናቀቀ ሲሆን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለምረቃ በቅቷል።

ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ መጠናቀቃቸው ምን አንድምታ እንዳለው ኢዜአ የተለያዩ ሰዎችን አነጋግሯል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ ከለውጡ በፊት በርካታ ፕሮጀክቶች ተጀምረው ባለመጠናቀቃቸው የሀገርና የህዝብ ሀብት ይባክን እንደነበር ጠቅሰዋል።

ከለውጡ ወዲህ ሀገሪቱ በርካታ ችግሮችን እየተጋፈጠችም መንግስት ለእነዚህ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በሰጠው ትኩረት በተባለላቸው ጊዜ ተጠናቅቀው አገልግሎት ሲሰጡ እየተመለከትን ነው ብለዋል።

የአዲስ አበባ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ዶክተር ሀና የሺንጉስ በበኩላቸው ሀገራዊ ፋይዳ ያላቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶች በታለመላቸው ጊዜ መጠናቀቅ መቻላቸው የመንግስትን የመፈፀም ብቃትና አቅም እንደሚያሳይ ተናግረዋል።

የውስጥና የውጭ ጠላቶች ተቀናጅተው ኢትዮጵያን ለማጥፋት ዘመቻ በከፈቱበት ወቅት ችግሮችን ተቋቁሞ እንዲህ አይነት ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክት ማስመረቅ የአመራር ቁርጠኝነት ነው ያሉት ደግሞ አርቲስት ስለሺ ደምሴ ናቸው።

ለዚህ ደግሞ በተለይ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ላሳዩት የአመራር ቁርጠኝነት ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል ነው ያለው።

የአዲስ አበባ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ግርማ ሰይፉ በበኩላቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ ብቻ ሳይሆን መጠበቅና መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባዋል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም