በሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ የቦንብ ጥቃት የተጠረጠሩት አቶ ጥላሁን ጌታቸውና ብርሃኑ ጃፋር ላይ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደ

90
አዲስ አበባ ነሀሴ 21/2010  በሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ የቦንብ ጥቃት በተጠረጠሩት አቶ ጥላሁን ጌታቸውና ብርሃኑ ጃፋር ላይ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የተጨማሪ 14 ቀናት የምርመራ ጊዜ ፍርድ ቤቱ ፈቀደ። የፌዴራሉ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ተረኛ ወንጀል ችሎት በሰኔ 16 በመስቀል አደባባይ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ወቅት በደረሰው የቦንብ ጥቃት፤ ቦንብ በማቀበልና በመወርወር ተጠርጣሪዎች አቶ ጥላሁን ጌታቸውና አቶ ብርሃኑ ጃፋርን ጉዳይ ዛሬ ተመልክቷል። ጉዳዩን የያዘው መርማሪ ፖሊስ እንዳስረዳው በተጠርጣሪዎቹ አቶ ጥላሁን ጌታቸውና ብርሃኑ ጃፋር እስካሁን በርካታ ምርመራዎችን ሲያካሄድ ቆይቷል። ነገር ግን የጥቃት ወንጀሉ ውስብስብ በመሆኑ ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግ ተጨማሪ ጊዜያት አስፈልጎታል። ለተጨማሪ ጊዜ ምርመራ ከጠየቀባቸው ምክንያቶች መካከልም የተጠርጣሪዎችን የስልክ ልውውጥ ከኢትዮ-ቴሌኮም መቀበልና የኤፍ ቢ አይ ምርመራ ውጤትን መመልከት በሚል ጠቅሷል። የቦንብ ጥቃቱን በማስተባበር፣ ሰዎችን በመመልመልና ቦንብ በራሳቸው መኪና ጭነው ወንጀል ወደተፈፀመበት ቦታ በመውሰድ በሽብርተኝነት የተጠረጠረው አቶ ብርሃኑ ጃፋር ጠበቃ፣ መርማሪ ፖሊስ የጠየቀበት ምክንያት በቂና አሳማኝ ባለመሆኑ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል። በዚህም ደንበኛቸው የዋስትና መብት ተሰጥቶት ጉዳዩን በውጭ ሆኖ እንዲከታተል ተክራክረዋል። መርማሪ ፖሊስ በበኩሉ ተጠርጣሪው በተለያዩ የስልክ መስመሮች ሲጠቀም እንደነበር በመጥቀስ ተጨማሪ ምርምራ እንደሚያስፈልገውና ሽብርተኝነትን ደግፎ ሲንቀሳቀስ እንደነበር የሚያሳዩ መረጃዎች እንዳሉት ጠቅሷል። ስለሆነም የተጠረጠረበት ሽብረርተኝነት ከመሆኑ በተጨማሪ ተጠርጣሪው ቢለቀቅ አደጋ ሊያደርስ ይችላል በሚል የዋስትና ጥያቄው ውድቅ እንዲደረግ ነው የጠየቀው። ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ያቀረበውን ምክንያት በመቀበልና የወንጀሉን ውስብስብነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጠርጣሪዎችን ዋስትና ውድቅ በማድረግ ተጨማሪ የምርመራ ጊዜውን ፈቅዷል። በዚህም ፍርድ ቤቱ የመርማሪ ፖሊስን የምርመራ ውጤት ለመስማት ለጷጉሜ 5 ቀን 2010 ዓ.ም ቀጠሮ ይዟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም