በክልሉ ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት ተጠናቋል

75

ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሀረሪ ክልል ከውጭ የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል አስፈላጊውን ዝግጅት መጠናቀቁን የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ገለጸ። የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ጥሪ ተከትሎ ከተለያዩ የአለም ሀገራት ወደ ሀገር ቤት የሚመጡ ሀገር ወዳድ ዳያስፖራዎችን ለመቀበል እና በክልሉ በሚኖራቸው ቆይታቸው የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቁቁን የክልሉ መንግስት አስታውቋል።

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንደገለጹት ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተደረገላቸው ጥሪ መሰረት ወደ ሀገር ቤት እየገቡ ያሉ እንግዶችን ተቀብሎ ለማስተናገድ በክልሉ በኩል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል። የእንግዶቹ ወደ ክልሉ መምጣትም በኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና አሸባሪው ህወሓት በሀገር ላይ በከፈተው ጦርነት ምክንያት የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲነቃቃ ከማድረግ አንፃር ፋይዳው የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ወደ ክልሉ የሚመጡ የዲያስፖራ ማህበረሰብ በቆይታቸው ጥሩ መስተንግዶና አገልግሎት እንዲያገኙ የክልሉ መንግሥት ከነዋሪው በተለይም ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛልም ነው ያሉት።

"የምንቀበለው በትግል ላይ የቆዩ ጀግኖችን ነው" ያሉት አቶ ሔኖክ የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ ለማስተናገድ ከሆቴል ቤቶችና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው በክልሉ ለሚኖራቸው ቆይታ ሆቴል ቤቶች ከ30 እስከ 50 በመቶ ቅናሽ በማድረግ ለማገልገል መዘጋጀታቸውን አክለው ገልጸዋል። ክልሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉት እና ለቱሪስት ምቹ ክልል መሆኗን ጠቅሰው ቀልጣፋ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

እንግዶቹ በክልሉ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

በክልሉ በሚገኙ የተለያዩ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለሚሳተፉ ዲያስፖራዎችም የክልሉ መንግሥት አስፈላጊውን ምቹ ሁኔታዎችን ስለመፍጠሩም አንስተዋል።

ሀገራዊ ጥሪውን ተከትሎ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ እንግዶች ወደ ክልሉ ሲመጡም በእንግዳ ተቀባዩ ህዝባችን ደማቅ አቀባበል ይጠብቃቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም