ኢትዮጵያውያንን በበጎ አድራጎት ስራዎች የሚደግፉት ግለሰብ የብሪትሽ ኢምፓየር ሜዳልያን ተሸለሙ

138

ታኅሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) “ሆፕ ኢትዮጵያ” በሚል ተነሳሽነት ኢትዮጵያውያንን በበጎ አድራጎት ስራዎች የሚደግፉት ግለሰብ የብሪትሽ ኢምፓየር ሜዳልያን ተሸለሙ።

ማይክ ኪንግ ይባላሉ። እ.አ.አ በ2004 ባለቤታቸው አንጂ ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት መጥተው ከተመለሱ በኋላ በተለያየ ችግር ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦችን ለመደገፍ ሀሳብ ይወጥናሉ።

ከዛ ጊዜ ጀምሮ ጥንዶቹ ከ2 መቶ 50ሺህ ዩሮ በላይ በማሰባሰብ ኢትዮጵያውያንን በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች እየደገፉ ይገኛሉ።

“ይህን ሀሳባችንን ለሰዎች ነግረን ድጋፍ እንደሚያደርጉልን ሲነግሩን “ሆፕ ኢትዮጵያ” በሚል ፕሮጀክት ቀርጸን በየ አመቱ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የበጎ አድራጎት ስራዎቹን እየሰራን ነው” ብለዋል ከሽልማቱ በኋላ ማይክ ኪንግ ለማልዶን ስታንዳርድ በሰጡት አስተያየት።

እስከ ዛሬ ባሰባሰብነው ድጋፍ አራት መቶ ሰዎች የመብራት ሃይል ተጠቃሚ ሆነዋል ያሉት በጎ አድራጊው፤ በድጋፉ ስራ ፈላጊ ዜጎች ስራ እንዲያገኙ መደረጉን፣ የህክምና ቁሳቁሶች አቅርቦትና የውሃ መስመር ዝርጋታ መከናወኑን እንዲሁም ለልጆችና እናቶች ደግሞ ልዩ ልዩ ድጋፎች መደረጋቸውን አንስተዋል።

የእንግሊዝ ንግስት የ2022 አዲስ ዓመት መግባቱን አስመልክቶ የብሪትሽ ኢምፓየር ሜዳልያ አሸናፊዎችን ዝርዝር በገለጹበት ወቅት ስማቸው ሲጠራ ሲሰሙ የተሰማቸውን ስሜት የተናገሩት ማይክ ኪንግ “ለዚህ ሽልማት መታጨቴን ሳውቅ ደንግጬ ነበር፣ በዚህ መልኩ እውቅና ይሰጠኛል ብዬ አስቤው አላውቅም” ብለዋል።

የብሪትሽ ኢምፓየር ሜዳልያ ሽልማት እ.አ.አ ከ1917 ጀምሮ በወታደራዊ ወይም በሲቪል ዘርፍ በጎ አስተወጽኦ ላበረከቱ ግለሰቦች በንጉሳውያኑ ቤተሰቦች የሚሰጥ ታሪካዊ እውቅና ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም