ሀገር አቀፍ ምክክሩ በፖለቲካ ልሂቃኑ እና በህዝቦች መካከል ብሔራዊ መግባባት የሚፈጠርበት እንጂ ከአሸባሪዎች ጋር ድርድር የሚካሄድበት አይደለም - አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን

103

ታህሳስ 23 ቀን 2014 (ኢዜአ) ሀገር አቀፍ ምክክሩ በህዝቦች መካከል ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አላማ ያለው እንጅ ከአሸባሪዎች ጋር መደራደርን ታሳቢ ያደረገ አይደለም ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን አስታወቁ።

ሚኒስትር ዴኤታው በፈረንጆች 2021 ከኢትዮጵያ አለማቀፍ ግንኙነት ጋር በተያያዘ የተሰሩ ስራዎችን እና በቀጣይ 2022 የትኩረት አቅጣጫዎችና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ከ"ሆርን ሪቪው" ጋር ቆይታ አድርገዋል።

አምባሳደር ሬድዋን በዚህ ወቅት የውስጥ ችግሮችን መፍታት የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም እንደሚያስችል አስገንዝበው በቅድሚያ ብሔራዊ መግባባት በሚለው ሀሳብ ላይ ግልጽነት ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ይደረጋሉ ተብለው የታሰቡት አገራዊ የምክክር መድረኮች በህዝቡ እና በፖለቲካ ልሂቃኑ መካከል የጋራ መግባባት ማስፈንን ታሳቢ ያደረገ ነው፤ ይህ ማለት ግን አሸባሪ ከተባሉ አካላት ጋር መደራደር ማለት አይደለም ብለዋል።

የህውሃት ስሪት ለአመጽ እንጅ ለሰላም የሚመች አይደለም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፥ የየትኛውም ሀገር መንግስት ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ሲደራደር አይተን አናውቅም እኛም፤ አንደራደርም ነው ያሉት።

የመደበኛ እና መልሶ ማቋቋም ስራዎችን አጠናክሮ ለመቀጠል ግልጽ ሁኔታዎችን እና ደረጃዎችን ማውጣት የኢትዮጵያ መንግስት ሃላፊነት መሆኑንም ማንሳታቸውን ከብልፅግና ፓርቲ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም