የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት የአቶ አብዲ መሀመድ ኡመር ያለመከሰስ መብት አነሳ

60
ጅግጅጋ ነሀሴ 21/2010 የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባኤ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት የአቶ አብዲ መሀመድ ኡመርና የሌሎች ስራ ኃላፊዎችን  ያለመከሰስ መብት አነሳ፡፡ አቶ ሙስተፌ መሀሙድ ዑመርን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ተሹመዋል፡፡ ምክር ቤቱ ትናንት አመሻሻ ላይ ባካሄደው በዚሁ አስቸኳይ ጉባኤው ርዕስ መስተዳድር ከነበሩት ሌላ  የስድስት ስራ ኃላፊዎችን ያለመከሰስ መብት አንስቷል፡፡ እነዚህ ስድስት የስራ ኃላፊዎች 1/የክልሉ ጠቅላይ ዓቃቤ ህግና ፍትህ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዲጀማል ቀሎንቢ፣ 2/የሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ራህማ መሀሙድ 3/ የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብራሂም መሀድ 4/የውሃ ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴቅ አብዱላሂ 5/ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ኢብራሂም መሀሙድ ሙባሪክ እና 6/የኢሶህዴፓ የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ኡመር አብዲ ናቸው፡፡ የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ መሀመድ ረሼድ ኢሳቅ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ምክር ቤቱ በግለሰቦቹ ላይ ያለመከሰስ መብትን ያነሳው ዋና ምክንያት በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ቀውስ እጃቸው እንዳለበት በመረጋገጡ በህግ እንዲጠየቁ ለማድረግ ነው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ምክር ቤቱ አቶ ሙስተፌ መሀሙድ ዑመርን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አድርጎ ሾሟል፡፡ ምክር ቤቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩን የሾመው በኢሶህዴፓ አቅራቢነት በሙሉ ድምጽ ሲሆን ተሿሚው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላሂ ኡጋዝ መሀሙድ አማካኝነት ቃለ መሀላም ፈፅመዋል፡፡ አቶ ሙስተፌ መሀሙድ የኢትዮጵያ ሶማሊ ህዝብ ዴሞክራሳዊ ፓርቲ (ኢሶህዴፓ)  በቅርቡ በአዲስ አበባ ባካሄደው ሰብሰባ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው መመረጣቸውም ታውቋል፡፡ በተጨማሪም የክልሉ ምክር ቤት አስቸኳይ ጉባኤ  በቅርቡ አጽድቆት የነበረው  የ99 ወረዳዎችና የ22 ከተማ አስተዳደሮችን በመሻር በቀድሞ አደረጃጀት መሰረት እንዲቆይ ወስኗል፡፡ የወረዳዎቹን አስፈላጊነት ጥናት ሳይደረግ  በክልሉ የሚገኙ ጎሳዎች መካከል ግጭት ለመቀስቀስ የቀድሞ የክልሉ አመራር ግፊት የፀደቁ በመሆናቸው ሁኔታዎችን ለማስተካከል መሻሩን የምክር ቤቱ አባል አቶ አህመድ አብዲ ገልጸዋል፡፡ ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ ከድር አብዲ በበኩላቸው " ምክር ቤቱ በአንድ ጊዜ ያፀደቃቸው ወረዳዎች እና ከተማ አስተዳደሮች በምንም መልኩ ሊተገበር እንደማችል ህዝቡ ራሱ ይገነዘባል "ብለዋል፡፡ ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ ሰፊ ክርክር ካደረገ በኋል አካሄዱ ህግን ያልተከተለ መሆኑን በመገንዘብ በሙሉ ድምፅ ሽሮታል፡፡ በዚህም የክልሉ ወረዳዎች ቀድሞ ወደ ነበሩበት 93 እና የከተማ አስተዳደሮችም  ስድስት  ሆነው እንዲቆዩ ተወስኗል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም