በክልሉ የፍኖተ ብልጽግና እቅድን ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል

238

ጋምቤላ ፤ታህሳስ 22/2014 (ኢዜአ) የህዝብን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በሚመልስ መልኩ የተዘጋጀውን የፍኖተ ብልጽግና እቅድ ለማሳካት አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ አሳሰቡ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች የአስር ዓመት የልማትና የመልካም አስተዳደር እቅዶች ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ ባለፉት ዓመታት ህዝቡ  የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ሲያነሳ ቆይቷል።

የህዝቡን ጥያቄዎች ምላሽ በሚሰጥ መልኩ የፍኖተ ብልፅግና እቅድ መዘጋጀቱን አመልክተው፤ ይህንን  ውጤታማ በማድረግ ለማሳካት አመራሩ  በቁርጠኝነት ሊሰራ  እንደሚገባ አሳስበዋል።

በክልሉ ያለው ውስን በጀት በአግባቡ በመምራት ረገድም በትኩረት መስራት እንዳለበት የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የገቢ አማራጮችን አሟጦ በመጠቀም የገቢ አቅምን የማሳደጉ ተግባርም ሌላው የአመራሩ ትኩረት አቅጣጫ ሊሆን እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተንኳይ ጆክ በበኩላቸው፤ የአስር ዓመቱ የልማት እቅድ የክልሉን የሰው ኃይልና የተፈጥሮ ሀብት ግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ያለውን የመሬት፣ የውሃ፣ የማዕድንና ሌሎች የተፈጥሮ ሀብቶችን ወደ ልማት መለወጥ ከተቻለ የተፈለገውን የልማት ግብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ማሳካት ይቻላል ብለዋል።

እቅዱን ስኬታማ ለማድረግ ተገቢ ያልሆኑ ወጪዎችን በመቀነስ በጀትን ለታለመለት ዓላማ ማዋል እንደሚገባ ያመለከቱት ደግሞ የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡቦንግ ኡቶው ናቸው።

በክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ አዘጋጅነት ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ሴክተር መስሪያ ቤቶች አመራሮች  ተሳትፈዋል።