በእሳት አደጋ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወደመ

147

ሆሳዕና ፤ ታህሳስ 22/201 (ኢዜአ) በሆሳዕና ከተማ ትናንት ሌሊት በተከሰተ የእሳት አደጋ ከ10 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው ንብረት መውደሙን ፖሊስ አስታወቀ።

በአደጋው በሰው ህይወት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተመልክቷል።

በከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ  የህዝብ ግንኙነት ማስተባበሪያ ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ካሳ ሊዕሊሶ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ የእሳት አደጋው የደረሰው  በከተማው ሊች አምባ መንደር 1 በተለምዶ ታይዋን ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ትናንት ሌሊት አምስት ሰዓት ተኩል አከባቢ ነው።

በአደጋው አስር የልብስ ስፌት አገልግሎት መስጫ ክፍሎች፣ አልባሳት ና የልብስ መስፊያ ማሽኖች ሙሉ ለሙሉ መውደማቸውን  ጠቁመዋል።

የእሳት ቃጠሎው ወደ ሌሎች ቤቶች እንዳይዛመትና የከፋ ችግር እንዳያስከትል ህብረተሰቡና የፀጥታ አካላት ባደረጉት የተቀናጀ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉን ተናግረዋል።

አደጋው በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደሌለ ያመለከቱት  ዋና ኢንስፔክተር ካሳ፤  የወደመው ንብረትም ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚገመት አስታውቀዋል።

የእሳት አደጋው መንስዔ ለጊዜው ባይታወቅም ፖሊስ ጉዳዩን አስመልክቶ  ምርመራ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ  ከመሰል አደጋዎች እራሱን እንዲጠብቅም ዋና ኢንስፔክተሩ  አሳስበዋል።