“አሜሪካ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀቦችን ከጣለች ግንኙነታችን ሙሉ በሙሉ ያበቃለታል”- ፕሬዚዳንት ፑቲን

205

ታህሳስ 22 ቀን 2014 (ኢዜአ) “አሜሪካ በሩሲያ ላይ አዲስ ማዕቀቦችን ከጣለች የሁለቱ ሀገራት የሻከረው ግንኙነት ሙሉ ለሙሉ ይቋረጣል” ሲሉ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስጠነቀቁ።

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እና የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን በወቅታዊ የሩሲያና ዩክሬን ጉዳይ ላይ የስልክ ውይይት አድርገዋል።

ለረጅም ደቂቃዎች የተካሄደው የሁለቱ መሪዎች ውይይት መረጋጋት የታየበት ሆኖም ማስጠንቀቂያዎች የታከሉበት ነበር ተብሏል።

አሜሪካ ማዕቀብ የመጣል ውሳኔ ካላት ትልቁ ስህተቷ እንደሚሆን የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን መናገራቸውን አር ቲ አስነብቧል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በበኩላቸው ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጥቃት የምትከፍት ከሆነ አሜሪካ እና አጋሮቿ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።

ሩሲያና ዩክሬን ከሰሞኑ በድንበር የጸጥታ ስጋት እየተወቃቀሱ መሆናቸው ይታወቃል።

ዩክሬን የሩሲያ 100 ሺህ የጦር ሠራዊት በምስራቃዊ ድንበር ሰፍሯል፤ ይህ ጥቃት ሊፈፀምብኝ ይችላል የሚል ስጋቷን ገልጻለች።

በአካባቢው ያለውና አሜሪካ ይሁንታ የሚንቀሳቀሰው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) የጥምር ጦር በሩሲያ ላይ የፀጥታና ደህንነት ስጋት መደቀኑን ሞስኮ ስትገልፅ ሰነባብታለች።

ፕሬዚዳንት ፑቲን “ኔቶ”ን እና አሜሪካን ባስጠነቀቁበት ንግግራቸው ሩሲያ በግዛታዊ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ላይ የደህንነት ስጋት እንደማይፈጥር የማረጋገጫ ሰነድ ያስፈልጋታል ብለዋል።

ሆኖም የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን የሩሲያ ስጋት እንደሚያሳስባቸው ገልጸው፥ ወደ ስምምነት የሚያስገባ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ እንቸገራለን ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም