በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ያለ ልዩነት ለክልሉ ብልፅግና እንዲሰሩ ጥሪ ቀረበ

64
አዲስ አበባ ነሃሴ 21/2010 በሶማሌ ክልል የሚኖሩ ዜጎች ያለ ልዩነት ለክልሉ ብልፅግና እንዲሰሩ በውጭ አገር የሚኖሩ የክልሉ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጥሪ አቀረቡ፡፡ የክልሉ ነዋሪዎች ግለሰቦች ላይ የሚደረግ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን እንዲታገሉም አሳስበዋል፡፡ በአሜሪካ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች "ዱልሚቲት" በሚል ስያሜ ተደራጅተው በክልሉ የሚፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ሲታገሉ ቆይተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለዲያስፖራው ያቀረቡትን ጥሪ ተከትሎ የዱልሚቲት አመራሮች ከበርካታ ዓመታት በኋላ ወደ ክልላቸው ገብተዋል፡፡ ኢዜአ በጅግጅጋ በመገኘት አመራሮቹን ባነጋገረበት ወቅት እንዳሉት፤ የክልሉ ነዋሪዎች ከጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አውሮፕላን ማረፊያ ጀምሮ በቆይታቸው እያደረገላቸው ያለውን ድጋፍ አድንቀዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ ብሎም በኢትዮጵያ እየታዩ ያሉ የለውጥ እንቅስቃሴዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን አውስተው፤ የክልሉ ነዋሪዎች ተደጋግፈው ለሁለንተናዊ ለውጥ መስራት እንዳለባቸው ነው የጠቆሙት፡፡ የዱልሚቲት ሊቀ-መንበር አቶ ኡመር ዳሆልርሲ ሁሉም የክልሉ ነዋሪ በአንድነት ከሰራ የማይቻል ነገር የለም ይላሉ፡፡ ጎሳን ሳይሆን ዕውቀትን መሰረት በማድረግ ያለመድልዎ የስራ ዕድል ሊመቻች እንደሚገባም ጠቁመዋል። ክልሎች የሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ መሆናቸውን ተቀብሎ መከባበር እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የዱልሚቲት አፈ-ጉባኤ በሽር ገራድ አህመድ ናቸው፡፡ ሁሉም የክልሉ ነዋሪ የትኛውንም አይነት የመብት ጥሰት እንዲሁ ማለፍ እንደሌለበትም ተናግረዋል፡፡ በእንግሊዝ አገር ሲኖሩ በማህበራዊ ሚዲያ ስለክልሉ ፖለቲካዊ ሁኔታ በመጻፍ የሚታወቁት አቶ አብደልረሽድ አሊ በበኩላቸው "በውጭ አገራት የሚኖሩ ዘመዶቻችሁ ተቃዋሚ ናቸው በሚል ምክንያት ብቻ እንግልት የሚደርስባቸው የክልሉ ነዋሪዎች ነበሩ" ሲሉ ተናግረዋል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልሉ እየታዩ ባሉ ለውጦች ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ በቀጣይ ክልሉን የሚያስተዳደር አካል ለዜጎች መብት መከበር ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም