የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ወደ ምርምር ተቋምነት እንዲቀየር ተወሰነ

88
አዲስ አበባ ነሀሴ 21/2010 የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ተልዕኮውን ሲያጠናቅቅ የምርምር ተቋም ሆኖ እንዲቀጥል መወሰኑን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ ተናገሩ። የከተማዋን ትራንስፖርት ለማዘመን ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ በ10 አመት ውስጥ መሰረታዊ የሆነ የትራንስፖርት ምላሽ ለመስጠት የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት አቋቁሞ እየሰራ ይገኛል። የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊና ምክትል ከንቲባው ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ፅህፈት ቤቱ የትራንስፖርት ዘርፉን የመምራት አቅም ጠንካራ እንዲሆን አልሞ እየሰራ ነው። ዘመናዊ መሰረተ ልማቶችን የማስፋፋትና የዘርፉን ቴክኖሎጂዎች የማላመድ ስራ የፅህፈት ቤቱ ተግባር እንደሆነ ገልፀዋል። ከ2006 ዓ.ም ጀምሮ ባለው አስር አመት አንገብጋቢ የሆኑ ችግሮችን የመፍታት አቅም መኖሩን የሚያመላክት ፍንጭ መታየቱን ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ገልጸዋል። በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ አውቶቡሶች ብቻ የሚጓጓዙባቸው መንገድ በመገንባት ከተማዋ የዘመናዊ ትራንስፖርት ተጠቃሚ እንደምትሆን ጠቁመዋል። መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነና አሁን እየተፈጠረ ያለው የገንዘብ አቅምና የመንግስት ቁርጠኝነት በዚሁ ከቀጠለ የአዲስ አበባ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ለአፍሪካ ከተሞች ምሳሌ መሆን ይችላል ብለዋል። ትራንስፖርቱን የማዘመን ስራ የሚሰራውና ለ10 አመት የተቋቋመው የትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ጊዜው ሲጠናቀቅ ወደ ምርምር ተቋምነት እንዲቀየር መወሰኑንም ተናግረዋል። በመንገድ ዘርፍ ምርምር የሚያደርግና ቴክኖሎጂዎችን የሚያላምድ ተቋም እንደሚሆን ነው የገለፁት። ፈጣን የአውቶብስ መንገድ ለመገንባት ሰባት ዋና ዋና መስመሮች ተለይተው የዲዛይንና የገንዘብ የማፈላለግ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ዘመናዊ ተርሚናሎች ዲፖዎች፣ የአዲስ አበባ ትራፊክ መቆጣጠር የሚያስችል መዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ባለፈው ከአንድ ወር በፊት አስቀምጧል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም