"ግፍ የፈጸሙብኝን የእጃቸውን ይስጣቸው ብዬ ለፈጣሪ ትቻለሁ" - በአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች የተደፈሩት መነኩሲት

74


ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ግፍ የፈጸሙብኝን የእጃቸውን ይስጣቸው ብዬ ለፈጣሪ ትቻለሁ" ይላሉ በአሸባሪው ህወሃት ታጣቂዎች የተደፈሩት የራያ ቆቦዋ የ70 አመት መነኩሲት፡፡
የሕወሃት ወራሪ ሃይል በአማራና አፋር ክልሎችም በየደረሰበት ስፍራና አጋጣሚ ሁሉ ቁሳዊ ውድመት እና ኢ-ሰብዓዊ ግፍና ሰቆቃ አድርሷል።

አንዳንዳዶቹ ግን በተለይም በኢትዮጵያዊ እሴት ቅኝት ሲታሰቡ ሰሚን ግራ ሚያጋቡ፣ ለማመን የሚከብዱ፣ ማድረግ ቀርቶ ማሰብን የሚዘገንኑ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች ለሽብር ቡድኑ ሰራዊት ዕለታዊ እኩይ ተግባራት ሆነዋል።

የአረመኔው ቡድኑ ግፍና ሰቆቃዎች በጅምላ ግድያ፣ በተራ አስገድዶ መድፈርና ቁሳዊ ውድመት ቃላት የሚዘለሉ ሳይሆን ለአእምሮ የሚከብድ የስነ ልቦና ጠባሳ የጣሉ፣ በታሪክ የሚያሳፍሩ አይገመቴ የርኩሰት ጾታዊ ጥቃቶች ከታዳጊዎች እስከ መነኮሳት ተፈጽመዋል።

ከተፈጸሙ የንጹሃን ግድያዎች ከዓለማዊ የስነ ልቦናዊ ጉዳቶች ባሻገር በሃይማኖት አስተምህሮ ለዘላለማዊ መንፈሳዊ ህይወት የማይጠገኑ ጥቃቶች በመነኮሳት ላይ ተፈጽሟል።

ሴት አያቶች የልጅ ልጆቻቸው በሚሆኑ የአሸባሪው ቡድን አባላት በቡድን ተደፍረዋል።

ኢዜአ በራያ ቆቦ ቆቦ ከተማ ተገኝቶ ያነጋገራቸው የ70 አመት አዛውንትም በሽብር ቡድኑ አስነዋሪ ተግባር ሰለባ ከሆኑት መነኮሳት አንዷ ናቸው።

'ዓለም በቃኝ' ብለው ሰማዊያዊ አምላካቸውን ለማመስገንና ለመማጸን ደጀ ሰላም መመላለስ የሰርክ ግብራቸው ያደረጉት እኚህ መነኩሲት፤ በምግባረ-ቢሶች በቡድን ተደፍረው ለስነ ልቦና ጉዳት ተዳርገዋል።

ድርጊቱ የፈጸመበትን ሁነት ሲያስታውሱ በአንዲት የተረገመች ዕለት ምሽት አገር አማን ብለው ባረፉበት ሁለት አሸባሪ አባላት የመነኩሲቷን ደካማ የጎጇቸውን በር ገንጥለው ስለመግባታቸው ይናገራሉ።

"ማነው ብዬ ደንግጬ ከመኝታዬ ስነሳም አንዱ አፌን አፈነኝ ባለሁበትም ወደቅኩ" ይላሉ እማሆይም ሳግ እየተናነቃቸው።

"እባካችሁ መነኩሴ ቆራቢ ነኝ ብዬ መስቀሌን አሳይቼ ብለምናቸውም በግዴታ ለሁለት ተፈራርቀው ደፈሩኝ" ሲሉ የአረመኔዎች የርኩሰትና የጭካኔ ጥግ ያወሳሉ።

"ሰው በላ ናቸው፤ ከሰው ፍጡር የማይጠበቅ ግፍ የፈጽሙ ወንጀለኞች" የሚሉት እኚህ አቅም ያጡት የግፍ ሰለባ እናት፤ “በኔ ላይ የደረሰውን በደል ለፈጣሪ ሰጥቻለሁ፤ ፈጣሪ የእጃቸውን ይስጣቸው” ይላሉ።

ክፉኛ በተጎዳ የእናት አንጀታቸው የሽብር ቡድኑን በእርግማን ያለፉት እኚህ እናት ግፍና በደልም አሸባሪው ቡድን ምክንያት በሌሎች የአማራና አፋር ክልል እናቶች ዕጣ ፈንታም ነበር።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም