ዳያስፖራው በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት የደረሰባቸውን ዜጎች ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ ሊያጠናክር ይገባል

277

አዲስ አበባ፣  ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን ጥሪ ተቀብለው ከተለያዩ ሀገራት አዲስ አበባ የገቡ ዳያስፖራዎች ዛሬ በወዳጅነት አደባባይ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በአቀባበል ሥነ ስርዓቱ ላይም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤና የተለያዩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

በመርሃ-ግብሩም አገር ውስጥ ምርቶች ለእይታ የሚቀርቡበትና ለሚቀጥሉት አስራ አራት ቀናት የሚቆይ አውደ ርዕይ ተከፍቷል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በዚህን ወቅት ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ማህፀነ ለምለም መሆኗን ባደረጋችሁት አኩሪ ተጋድሎ አስመስክራችኋል ነው ያሉት።

ባለፈው አንድ ዓመት ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ መሪ ተዋናይ ሆኖ መቆየቱን አንስተው፤ በተለይ  “በቃ” በሚል የተደረገው የፍታዊነት ትግል የዓለም ጥቁር ህዝቦችን ያነቃነቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ዳያስፖራው በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ለመደገፍና መልሶ ለማቋቋም እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክርም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

”ኢትዮጵያ በአንዳንድ የውጭ ሚዲያዎች በሀሰት ስሟ እንደሚነሳው እንዳልሆነች፤ ይልቁንም ልማት ላይ ያለች አገር መሆኗን ለቀሪው ዓለም እንድታሰገነዘቡ አደራ እላለለሁ ”ሲሉም ነው ያነሱት።

”በቀጣይም የኢትዮጵያን ገጽታ ለመገንባት ለምታደርጉት ጥረት የሚያግዛችሁ ስንቅ ይዛችሁ እንደምትሄዱ ሙሉ እምነት አለኝ” ብለዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገር ላቀረበችው ጥሪ ተግባራዊ ምላሽ በመስጠት እዚህ በመገኘታችሁ ታሪክ የማይዘነጋው ነው ብለዋል።

ይህ አጋጣሚ በአንድነትና በጋራ ሰርቶ ለማደግ ብሎም ወደ ብልጽግና ለመሸጋገር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር ነው ያሉት ከንቲባዋ፤ በመሆኑም በእልህና በቁጭት በጋራ ልንሰራ ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በመመከትና በማክሸፍ ረገድ ተደጋጋሚ ድል አስመዝግባችኋል ያሉት ከንቲባዋ፤ የአምባሳደርነት ሚናችሁን በአግባቡ ስለተወጣችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ዳይሬክተር ዶክተር መሀመድ እድሪስ፤ባለፉት ሦስት ዓመታት ዳያስፖራው በሀገሩ ጉዳይ የላቀ ሚና እንዲኖረው የተሰሩ ስራዎች አበረታች ውጤቶች ማስገኝታቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት ዳያስፖራው ማህበረሰብ በኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ ይበልጥ ተሳታፊ እንዲሆን ለማድረግም ኤጀንሲው በየደረጃው የሚያደርገው ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በተለይም ኢትዮጵያዊያኑ እና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ  ግንባታ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም ነው ያብራሩት።