የድሬዳዋን ሰላም ለማስጠበቅ ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተን እየሠራን ነው

213

ድሬዳዋ፤ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) የድሬዳዋን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ በሚከናወኑ ተግባራት ከፀጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው የድርሻቸውን እየተወጡ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናገሩ።


ነዋሪዎቹ ዓመታዊውን የቅዱስ ገብርኤል በዓልን ትላንት በድሬዳዋ በደመቀ ሥነ-ሥርዓት ባከበሩበት ወቅት እንዳሉት፣ የድሬዳዋ ነዋሪ ለዘመናት የሚታወቀው በአንድነትና በፍቅሩ ነው።


ይህን አንድነትና ፍቅሩን በመሸርሸር እርስበርስ ለማጋጨት የሚሯሯጡትን ፀረ-ሰላም አካላት ነዋሪው እንደማይታገስም ገልጸዋል።


የአካባቢን ሰላምና ፀጥታ መጠበቅ የእያንዳንዱ የድሬዳዋ ነዋሪ ኃላፊነት መሆኑንም ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።


ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ አብርሃም አለሙ፤ የአሸባሪው ህወሓትና ሸኔ ተላላኪዎች ድሬዳዋን የሁከትና የብጥብጥ ሜዳ ለማድረግ የሚያስወሩትን አሉባልታ ማንም ቦታ እንደማይሰጠው ገልጸዋል።

“እነዚህን አካላት ለህግ አሳልፎ በመስጠት ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድባቸው የበኩሌን እየተወጣሁ እገኛለሁ” ብለዋል፡፡


ወይዘሮ አልማዝ እንደሻው በበኩላቸው “አጊጠን አምረን በዓላትን የምናከብረው ሀገርና ሰላም ስላለን ነው፤ ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚሯሯጡ የአሸባሪዎቹ ህወሓትና የሸኔ ተላላኪዎችን ለህግ እናቀርባለን” ብለዋል፡፡


በምሽትና በቀን በተደራጀ መንገድ ከፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር የድሬዳዋን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ በመጠበቅ ላይ እንገኛለን ያሉት ደግሞ አቶ ሃያል ብርሃኑ ናቸው።


የሽብር ተልዕኮ ያነገቡትን አካላት ለፀጥታ ሃይሎች ፈጥኖ በመጠቆም ተገቢና ፈጣን እርምጃ እንዲወሰድባቸው በጋራ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡


በድሬዳዋ የቅዱስ ገብርኤል በዓል በተከበረበት ወቅት ጸጥታን ሲያስተባብሩ የነበሩ ወጣቶች ለድሬዳዋ ሰላምና የተጀመረው የፍቅር ጉዞ እንዲጠናከር ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ገልፀዋል።


ፀጥታን እያስከበሩ ከነበሩት መካከል ወጣት ኪሩቤል ፍቅሬሰላም ፤በአሸባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ ተላላኪዎች ሰላማቸው እንዳይበጠበጥ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ተናግሯል።


“በአንድ መንደር 50 ወጣቶች ተደራጅተን ከፖሊስ ጋር ሰላማችንን እያስከበርን እንገኛለን፤ የተለየ እንቅስቃሴ ስናስተውል ለሚመለከተው አካል እናሳውቃለን” ብሏል።


እንደ ወጣቱ ገለጻ፤ ሰላም በፀጥታ አካላት ብቻ የሚመጣ ሳይሆን የሁሉንም ነዋሪ አስተዋጽኦ የሚጠይቅ ነው።


የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ህዝብ ግንኙነትና የለውጥ ሥራዎች ዳይሬክተር ኮማንደር ገመቹ ካቻ በበኩላቸው፤ በድሬዳዋ በዓሉ ያለምንም ችግር በሰላም ተከብሮ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።


በየደረጃው ህብረተሰቡና ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር በመሆን ለሰላምና ፀጥታ መከበር እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ የሚመሰገንና ተጠናክሮ እንዲቀጥልም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡