የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

113

ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 3ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

3ኛ መደበኛ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ውሳኔዎች

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በ2014 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግስት ተጨማሪ በጀት እና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ2014 በጀት ዓመት በስራ ላይ እንዲውል ጠቅላላ ብር 561.7 ቢሊዮን ብር በጀት ማጽደቁ ይታወሳል፡፡

በወቅቱ ለበጀቱ ዝግጅት ታሳቢ የተደረጉ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ተለዋዋጭነት እንደተጠበቀ ሆኖ አሁን በአገራችን በተከሰተው ጦርነት ምክንያት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ እና ከኢኮኖሚ እንቅስቃሴ አኳያ የሚሰበሰበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠሩ እንዲሁም ወቅቱ የፈጠረውን የተጨማሪ ወጪ ፍላጎት በበጀት ሽግሽግ ለማስተናገድ ስላልተቻለ የተጨማሪ በጀት ጥያቄና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያ ተግባራዊ እንዲሆን በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የገንዘብ ሚኒስቴር አማካኝነት የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው አጀንዳ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ይጸድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል፡፡

2. በመቀጠል ምክር ቤቱ የተወያየው የነዳጅ ውጤቶች መሸጫ ዋጋ ማስተካከያና የታለመ ድጎማ አፈጻጸም የውሳኔ ሀሳብ ላይ ነው፡፡ ነዳጅ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ቁልፍ ሚና የሚጫወትና ከህብረተሰቡ የኑሮ ሁኔታ ጋር የተቆራኘ የሀይል ምንጭ በመሆኑ የችርቻሮ መሸጫ ዋጋው በኢኮኖሚው እና በህብረተሰቡ ላይ የጎላ ተጽእኖ እንዳይፈጥር በመንግስት እየተወሰነና ቁጥጥር እየተደረገበት ሲሰራበት ቆይቷል፡፡

ሆኖም የሀገሪቱን ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎችንና የህብረተሰቡን የኑሮ አቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት የሀገር ውስጥ የነዳጅ ችርቻሮ መሸጫ ዋጋ የዓለማቀፉን ዋጋ በሚያንጸባርቅ መልኩ እየታየና በየጊዜው እየተከለሰ ወደ ሸማቹ እንዲተላለፉ ባለመደረጉ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ እዳ በዋጋ ማረጋጊያ ፈንዱ ላይ እየተከማቸ ይገኛል፡፡

በመሆኑም ጎልተው የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ የነዳጅ ግብይት ሪፎርም በሀገር ደረጃ በእቅድ ተይዞ እየተከናወነ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ እየሰፋ የመጣውን በፖሊሲ ያልተደገፈ የነዳጅ ድጎማ ከተመረጡ ተሸከርካሪዎች በሂደት ለመቀነስና ለማስቀረት የሚያስችል የዋጋ ማስተካከያ ጥናት በማድረግ የቀረቡ የውሳኔ ሀሳቦችን ለመተግበር የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በቀረበው አጀንዳ ላይ ከተወያየ በኋላ የውሳኔ ሀሳቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ከዛሬ ጀምሮ ከስድስት ወር የዝግጅት ምዕራፍ በኃላ ተፈፃሚ እንዲሆን ወስኗል፡፡

3. ቀጥሎ የምክር ቤቱ የመወያያ አጀንዳ የነበረው የነዳጅ ውጤቶች የዋጋ ግንባታና ትርፍ ህዳግ አሰራር የውሳኔ ሀሳብ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በስራ ላይ ያለው የነዳጅ ዋጋ ማሻሻያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ መሰረት ላለፉት 25 ዓመታት በስራ ላይ ቆይቷል፡፡

ስለሆነም በመንግስት የተሰጠውን የፖሊሲ አቅጣጫ በተጠናከረና ውጤታማ በሆነ አኳኋን ለመተግበር እንዲቻል ነባሩ አሰራር ያለበትን ክፍተት መፈተሽና ማስተካከል አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ስለሆነም ላለፉት 25 ዓመታት በስራ ላይ የነበረውን አሰራር በማሻሻል ወጥነትና ግልጽነት ያለው የአሰራር ስርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ የውሳኔ ሀሳቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ከተወያያ በኋላ ውሳኔው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከፀደቀበት ከዛሬ ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

4. ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በድንጋይ ከሰል ማዕድን ልማት ላይ ከስምንት ድርጅቶች ጋር የሚያደረገው ስምምነቶች ምክር ቤት የተወያየበት ሌላው አጀንዳ ነው፡፡ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚገኙ የድንጋይ ከሰል ማዕድናትን አዋጭ በሆነ መንገድ በከፍተኛ ደረጃ የማምረትና የማበልጸግ ስራ በስምንት ኩባንያዎች የሚከናወን ሲሆን ኩባንያዎቹ ባቀረቡት የፕሮጀክት እቅድ መሰረትም በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ሀገራዊ ፍላጎትን ማሟላት የሚችል ምርት እንደሚያመርቱ ይጠበቃል፡፡

የፕሮጀክቶቹ ስምምነቶች ለመንግስትና ለአካባቢው ህዝብ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ተካተው ለምክር ቤቱ ቀርበዋል፡፡ ምክር ቤቱም በቀረበው ስምምነት ላይ ከተወያያ በኋላ ስምምነቶቹን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እንዲፈራረም ወስኗል፡፡

5. በመቀጠል ምክር ቤቱ ውይይቱን ያደረገው የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ረቂቅ አዋጅ ላይ ሲሆን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስርአት አስቀድሞ በሚደረግ አነስተኛ መዋጮ የጤና አገልግሎት ወጪ የሚሸፈንበት ስርአት ሲሆን የከፍተኛ ወጪ ስጋትን በመቅረፍና ፍትሀዊነትን በማረጋገጥ ሁሉም እንደህመሙ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ነው፡፡

በመሆኑም ከዚህ ቀደም ስርአቱ የሚመራበት በአዋጅ ደረጃ የወጣ የህግ ማዕቀፍ ያልነበረ በመሆኑ በፌዴራልና በክልል የአስተዳደር እርከኖች በተበታተነ መልኩ ሲሰራባቸው የነበሩትን የህግ ማዕቀፎች ወጥ ማድረግ በማስፈለጉ፣ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ትግበራ ሂደት በፌዴራልና በክልል አስፈጻሚ አካላት መካከል ግልጽ የስራ ክፍፍል እንዲኖርና በተቀናጀና በተናበበ ሁኔታ ስርአቱን ለመተግበር እንዲቻል ፍትሀዊ የጤና አገልግሎት አጠቃቀም እንዲኖር ለማድረግ ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ ይፀድቅ ዘንድ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መርቶታል፡፡6. በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን አላማና ተግባር ለመወሰን በወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በዋናነት በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ በርካታ የመንግስት ሀብቶችን ወደ አንድ ተቋም በመሰብሰብ እና ውጤታማ የኩባንያ አስተዳደር በመፍጠር ከእነዚህ ሀብቶች የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻልና ሀብቶቹን አሟጦ በመጠቀም የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ተወዳዳሪነት በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ ስትራቴጂካዊ የልማትና የኢንቨስትመንት መሳሪያ እንደሚሆን ታሳቢ በማድረግ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በደንቡ ላይ በስፋት ከተወያየ በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም