በክልሉ ከ 48 ሺህ 455 ሄክታር መሬት ላይ የሩዝ ሰብል ተሰብስቧል

85

ባህርዳር ፤ ታህሳስ 20/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በሩዝ ሰብል ከለማው ከ56 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት 48 ሺህ 455 ሄክታር ላይ ያለው ምርት መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ኤልያስ በላይ ለኢዜአ እንደገለፁት በክልሉ የሩዝ  ልማት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋና እያደገ መጥቷል።

የሩዝ ሰብሉ የለማው በክልሉ በመኽር ወቅቱ  በደቡብና ማዕከላዊ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎጃምና አዊ ብሄረሰብ ዞኖች ውስጥ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከለማው  56 ሺህ 534 ሄክታር መሬት  ውስጥ  85 ነጥብ 7 በመቶው  በወቅቱ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ባለሙያው እንዳሉት፤ በልማቱ እየተሳተፉ የሚገኙት 140 ሺህ የሚበልጡ አርሶ አደሮች ሲሆኑ የተሻሻሉ አሰራሮችና የምርት ማሳደጊያ ግብዓት እንዲጠቀሙ ተደርጓል።

ቀሪውን የሩዝ ሰብል እስከዚህ ወር መጨረሻ ሙሉ በሙሉ እንደሚሰበሰብ ጠቅሰው፤ ከለማው መሬትም ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል የሚበልጥ ምርት እንደሚጠበቅ  አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ  ጥራቱን የጠበቀ ምርት በማምረት ለገበያ እንዲያቀርብ ዘመናዊ የመፈልፈያ ማሽን በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመኽር ወቅት ከለማው መሬት የሚጠበቀው የሩዝ ምርትም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ጭማሪ ይኖረዋል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።

የደቡብ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ የሰብል ልማት ቡድን መሪ አቶ አስፋው ይልማ በበኩላቸው፤ በዞኑ የሩዝ ልማት መስፋፋት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት እያሳደገ መጥቷል ነው ያሉት።  

በዞኑ የጣና ኃይቅ የልማት ኮሪደር በሆኑት ፎገራ፣ ሊቦከምከምና ደራ ወረዳዎች ከ40 ሺህ  ሄክታር በላይ መሬት በሩዝ ሰብል መልማቱን ገልጸዋል።

አብዛኛው የእርሻ መሬት በክረምት ወቅት ውሃ የሚተኛበት በመሆኑ ከምርት ውጭ ሆኖ ያድር እንደነበርና በዚህም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ሳይሆን መቆየቱን አስረድተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የሩዝ ዝርያዎች  በማልማት ተጠቃሚነቱ እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።

''የሩዝ ልማት ከመጣ ወዲህ የምግብ ፍጆታችንን ከመሸፈን አልፈን የተሻለ ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል'' ያሉት ደግሞ በፎገራ ወረዳ የሽና ቀበሌ አርሶ አደር መልኬ መለሰ ናቸው።

በአንድ ሄክታር መሬት ላይ ያለሙትን የሩዝ ሰብል መሰብሰበ መጀመራቸውን ጠቅሰው፤ ከዚህም ከ55 ኩንታል በላይ ምርት  እንዲሚጠብቁ ተናግረዋል።

 በወረዳው የአቧና ኮኪት ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቸሬ መንግስት በበኩላቸው፤ የሩዝ ልማት ከመምጣቱ በፊት ክረምቱ ሲወጣ ጓያና ሽምብራ ያለሙ እንደነበር ገልጸዋል።

የሩዝ ልማት ከመጣ በኋላ በየዓመቱ አንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸውን  በማልማት ተጠቃሚ እንደሆኑም አመልክተዋል።

በመኸሩ ወቅት ያለሙት የሩዝ ሰብሉን አጭደው በማንሳትም በአሁኑ ወቅት በዳግም ልማት አጃ፣ ጤፍና ጓያ ሰብሎች ማልማት መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል።

በአማራ ክልል በ2012/2013 የምርት ዘመን በሩዝ ሰብል ከለማው 49 ሺህ 361 ሄክታር መሬት ላይ ከአንድ ሚሊዮን 689 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት መሰብሰቡን ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም