ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ በሚኖራችሁ ቆይታ ኢትዮጵያ የጽኑዎች አገር መሆኗን ለዓለም ሕዝብ በተግባር ማሳየት ይጠበቅባችኋል

69

ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ በሚኖራችሁ ቆይታ ኢትዮጵያ የጽኑዎችና የአይበገሬዎች አገር መሆኗን ለዓለም ሕዝብ በተግባር ማሳየት ይጠበቅባችኋል ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለጹ።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በዘላቂነት በማስከበርና መልሶ ግንባታ ሂደት ውስጥ ዳያስፖራው አገራዊ ሃላፊነቱን በተጠናከረ መልኩ እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን “የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ” ተቀብለው ለመጡ ዳያስፖራዎች የአቀባባል ስነ ስርዓት በወዳጅነት አደባባይ ተካሄዷል።

በስነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት አቶ ደመቀ ዳያስፖራው ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለይም ባለፈው አመት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መሪ ተዋናይ በመሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ለአገሩ ስለ ፍትህ በመሟገት አኩሪ ተግባር መፈጸሙን ገልጸዋል።

በ’በቃ’ ወይም ‘#NoMore’ የተደራጀ እንቅስቃሴ በማድረግ ለኢትዮጵያ አለኝታነቱን አሳይቷል፤ ለፓን አፍሪካኒዝም ሃይል ሰጥቷል፤ ለፍትሐዊነት የሚታገሉ ጭቁኖችን ትግል እንደ አዲስ ማደስ መቻሉን አመልክተዋል።

ዳያስፖራው ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ዘብ በመቆም ላከናወነው የጀግንነት ተግባር ሕዝብና መንግስት መኩራታቸውን ጠቁመዋል።

አሸባሪው ሃይል የኢትዮጵያን ክብርና ታሪክ ለማርከስ ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች ጸያፍ፣ አስነዋሪና እኩይ የሆነ ተግባር መፈጸሙን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን በተባበረ ክንድ አንገት ለአንገት በመተናነቅ መስዋዕትነት ከፍለው ታሪክ የማይረሳው አኩሪ ተግባር መፈጸማቸውንና የአገራቸውን ሉላዓዊነት ማስጠበቃቸውን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና ክብር ለመድፈር የሚፈልጉ ሃይሎችን ሴራ በማክሸፍ ጠንካራ አገር የመገንባት ብዙ የቤት ስራ መኖሩን በመግለጽ ትግሉ ገና መሆኑን አመልክተዋል።

ዳያስፖራው የሀሰት ፕሮፓጋንዳውን ከማክሸፍ አኳያ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረውም ተናግረዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በፍጥነት እየወጣች እንደሆነና በችግርና በፈተና ውስጥ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሯን እንዲሁም መደበኛ እንቅስቃሴዎቿን እያስቀጠለች እንደምትገኝ ማሳየት እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

“ሃይማኖታዊ በዓላቷን ማክበር የምትችል የጽኑዎችና የአይበገሬዎች አገር መሆኗን ማሳየት ይጠበቅባችኋል” ብለዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ የሚኖረው ቆይታ ለቀጣይ የዲፕሎማሲ ስራዎች ስንቅ እንደሚሆን የጠቀሱት አቶ ደመቀ፤ መንግስት ዳያስፖራው በሚኖረው ቆይታ ሰላሙና ደህንነቱ ተጠብቆ የተዘጋጀቱን የተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግ አስፈላጊውን ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጸዋል።ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የእናት አገራቸውን ጥሪ በአክብሮት ተቀብለው ወደ አገር ቤት ለመጡትና ለሚመጡት ዳያስፖራዎች ምስጋና አቅርበው ቆይታቸውም ውጤታማ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም