ጥሪው ዳያስፖራው ልቡ፣ መንፈሱና አካሉ ይበልጥ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተሳሰር ያደረገ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው

134

ታህሳስ 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የዳያስፖራው ወደ አገር ቤት ጉዞው ልቡ፣ መንፈሱና አካሉ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተሳሰር ያደረገ ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ ገለጹ።

የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ “የአንድ ሚሊዮን ዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ” ተቀብለው ለመጡ ዳያስፖራዎች የአቀባባል ስነ ስርዓት በወዳጅነት አደባባይ እየተካሄደ ነው።

በስነ ስርዓቱ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ሌሎች መንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሐመድ እንድሪስ የዳያስፖራው የአገር ቤት ጥሪ ዳያስፖራው መንፈሱ፣ ልቡ፣ አካሉ፣ ወኔውና ፍቅሩ ከኢትዮጵያ ጋር የተሳሰሩበት ታሪካዊ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

ጥሪው ለኢትዮጵያ ዘላቂ ድጋፍ የሚያደርግ ጠንካራ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ለመገንባት ለተጀመረው ስራ መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑን አመልክተዋል።

ዳያስፖራው ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ወቅት ውስጥ በሆነችበት ግዜ ለኢትዮጵያ ጠበቃ በመሆን ያሳየው የአገር ፍቅር የሚያስመግን ነው ብለዋል።

በቀረበው ጥሪ መሰረት በርካታ ዳያስፖራ ወደ አገር ቤት በመትመም ኢትዮጵያ ላይ የሚሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃ በተግባር ማጋለጡን ገልጸዋል።

ዶክተር መሐመድ ዳያስፖራውን እንኳን ወደ እናት አገራችሁ በሰላም መጣችሁ ብለዋል።

የ“አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ የአገር ቤት ጉዞ ጥሪ” የተመለከቱ መርሃ ግብሮች ከዛሬ ጀምሮ እስከ ጥር 15 ቀን 2014 ዓ.ም ይካሄዳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም