በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት የደረሰበት የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል በከፊል አገልግሎት መስጠት ጀመረ

61

ደሴ፤ ታህሳስ 20/2014(ኢዜአ) በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ዘረፋና ውድመት የደረሰበት የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል የተወሰነ ቁሳቁስ ተሟልቶለት በከፊል አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡

ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶክተር ተፈራ ጎበዜ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ሆስፒታሉ በህወሓት የሽብር ቡድን  ከሆስፒታሉ የሚችለውን ዘርፎ፣ መውሰድ ያልቻለውንም ሙሉ በሙሉ በማውደም ለህዝብ ያለውን ጥላቻ በግልጽ አሳይቷል።

አካባቢው ከወራሪው ቡድን ነጻ በወጣ ማግስት ሆስፒታሉን ሥራ ለማስጀመር በተደረገው ቅንጅታዊ ጥረት  የተወሰነ ቁሳቁስ ተሟልቶለት ካለፈው ሳምንት አንስቶ ለድንገተኛና ለወላድ እናቶች አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

እንዲሁም ከአለርት ሆስፒታል በተገኙ ማሽኖችና መድሃኒቶች ድጋፍም የቀዶ ሕክምና አገልግሎት መጀመሩንም ተናግረዋል።

በተያዘው  ሳምንት የተመላላሽ ሕክምና አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር የተጓደሉ የሕክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት በሙሉ አቅሙ ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ለእዚህም ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደሥራ መገባቱን ዶክተር ተፈራ አመልክተዋል።

በቅርቡ አስተኝቶ ማከምና ሌሎች መደበኛ ሕክምናዎችን ለመስጠት ከ90 በመቶ በላይ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ተሟልተው በእልህና በቁጭት ህብረተሰቡን ለማገልግል ወደ ስራ ማግባታቸውን አስረድተዋል።

የሆስፒታሉ የተኝቶ ሕክምና ክፍል ኬዝ አስተባባሪ ዶክተር ቁምላቸው መሰለ በበኩላቸው ፤ "የሽብር ቡድኑ ሆስፒታሉን ቢያወድመውም እውቀታችንና የሥራ ተነሳሽነታችንን መገደብ አልቻለም" ብለዋል።

በእልህና በቁጭት ያስጀመርነውን ሆስፒታል በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ እንዲገባ የሚጠበቅብንን ሁሉ እናደርጋለን ነው ያሉት።

ህብረተሰቡን ጭምር በማስተባበር የሆስፒታሉን አካባቢ በማጽዳት ለእይታ ምቹ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ ግብዓቶችን በማሰባሰብ ላይ እንደሚገኙም ጠቁመዋል።

"በቅርቡም የሕክምና አገልግሎቱን በተሻለ ሁኔታ በመስጠት ህብረተሰባችንን እንደምንክስና ጠላትን እንደምናሳፍር አልጠራጠርም" ብለዋል፡፡

ከኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች መካከል  አቶ አወል መሃመድ በሰጡት አስተያየት፤  ሆስፒታሉ በአጭር ጊዜ በከፊልም ቢሆን ሥራ በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው፤ በቀጣይም ሆስፒታሉን በቻሉት ሁሉ ለመደገፍና ለማስተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

"ቅንጣት ያህል ሰብዓዊነት የማይሰማው አሸባሪው ህወሓት በምንገለገልበት ሆስፒታል ላይ ጉዳት ቢያደርስም እኛ ተረባርበን በሙሉ አቅሙ እንዲንቀሳቀስ እናደርጋለን" ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የግንባታ ሥራው ለአስር ዓመታት ከተጓተተ በኋላ ባለፈው ዓመት ተጠናቆ ሥራ የጀመረው የኮምቦልቻ ጠቅላላ ሆስፒታል  ከአንድ ሚሊዮን ለሚበልጥ የአካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት አቅም እንደነበረው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም