አሜሪካ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚለው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካሄዷ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች ነው

114

ታህሳስ 20/2014/ኢዜአ/ የዩጋንዳው የዜና ድረ-ገጽ ፕላስ ኒውስ “ከኢትዮጵያ እስከ ሶማሊያ ዋሺንግተን ጣልቃ ገብነቷን ወደ ሶማሊያ አዙራለች” በሚል ርዕስ ባወጣው ዘገባ አሜሪካ እኔ ያልኩት ካልሆነ በሚለው የወጭ ጉዳይ ፖሊሲ አካሄዷ በመግፋት በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች መሆኑን ገልጿል።

አሜሪካ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ሞሐመድ የአገሪቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሐመድ ሁሴን ሮብሌን ከስልጣን ማገዳቸውን ማውገዟ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷን እንደሚጠቁም አንስቷል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም በሌሎች የአፍሪካ አገራት እንዳደረገችው ወገንተኛ በመሆን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ውሳኔን ማውገዟንና ድርጊቱም “አሳሳቢ” ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተአማኒነት ያለው ምርጫ እንዲካሄድ እያደረጉት ያለውን ጥረት እደግፋለሁ በሚል በውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቷ የአፍሪካ ጉዳዮች ቢሮ በኩል መግለጫ አውጥታለች።

ሶማሊያ የጀመረችውን የሰላም ጉዞ በሚያደናቅፉ አካላት ላይ እርምጃ እንደምትወስድም ገልጻለች።

በሶማሊያ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ትናንት ባወጣው መግለጫ ”የሶማሊያ መሪዎች ውጥረትንና ግጭትን ከሚያባብሱ ድርጊቶች መቆጠብ አለባቸው” ብሏል።

ለፕላስ ኒውስ ድረ-ገጽ አስተያየታቸውን የሰጡት ኡጋንዳዊው የአፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ ጀምስ ሩቦቢ”ጣልቃ ገብነት ሁልጊዜም የአሜሪካ የተለመደ ተግባር ነው፤ የአፍሪካ አገራትን ለማዳከም ለአንድ ወገን ትቆማለች ለምትፈልገው አካል ድጋፍ በማድረግ ከአጋሮቿ ጋር በመሆን የአገራትን ሀብት ትዘርፋለች” ብለዋል።

ሶማሊያ ለረጅም ጊዜ በፖለቲካ ቀውስ ውስጥ የነበረች አገር ናት አሁን ወደ ሰላም መንገድ እየመጣች ነው ያሉት ተንታኙ ይህን ጉዞ ለማደናቀፍ ለአንድ ቡድን በመወገን የሚደረግ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት የሌለው ድርጊት እንደሆነ ገልጸዋል።“ሶማሊያ ሉዓላዊ አገር ናት በምንም አይነት መንገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸውን ፕሬዚዳንት ብለው በመጥራት ወታደራዊ ሃይሎች ከፕሬዚዳንቱ ትዕዛዝ እንዳይቀበሉ እየፈጸሙት ያለው ድርጊት የሚወገዝ ነው” ብለዋል ጀምስ ሮቦቢ።

እንደዚህ አይነት ሕገ ወጥ ድርጊት እየፈጸመ ያለን ጠቅላይ ሚኒስትር በአደባባይ መደገፍ “አሳፋሪ ነው” ይሄ ጣልቃ ገብነት ካልሆነ ታዲያ ምን ሊባል ነው? ሲሉ ጥያቄ አዘል አስተያያታቸውን ሰጥተዋል።

የአሜሪካ መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፈጸሙት ለተባለው ድርጊት አይመርመሩ ንጹህ ናቸው የሚል አንድምታ ያለው እንደሆነም አመልክተዋል።

ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ሄርሜላ አረጋዊ በበኩሏ “አሜሪካ በሌሎች አገራት ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባቷን እንደተለመደ ጉዳይ አድርገን እናየዋለን” ስትል ገልጻለች።

የጥቂት ቡድኖችን ፍላጎት ለማሳካት በአገራት ላይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነትና እኔ ፈላጭ ቆራጭ ነኝ የሚለው አካሄዷን ማቆም አለባት ብላለች።

አሜሪካ በሶማሊያ ጉዳይ የያዘችውን አቋም የሚቃወሙ መልዕክቶች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ተጠቃሚዎች እየተላለፉ መሆኑን ፕላስ ኒውስ በድረ ገጹ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

አሜሪካዊው ጋዜጠኛና ደራሲ ኢዩጅን ፑርይር “አሜሪካ እ.አ.አ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ በሶማሊያ ሰላም እንዳይመጣ እንቅፋት ሆና ቆይታለች ኢምፔሪያሊስታዊ አካሄድ የሚያመጣው መፍትሔ የለም አሜሪካ ከሶማሊያ ላይ እጅሽን አንሺ” ብሏል።

ሌሎች ሰዎችም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት በኢትዮጵያ ላይ አልሳካ ያላትን ጣልቃ ገብነት በሶማሊያ እየሞከረች ነው፤ ጣልቃ ገብነትና የመንግስት ለውጥ አንቅበልም ብለዋል።

የአሜሪካ አካሄድ ሰላምን አያመጣም የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን ችግር በራሳቸው የመፍታት አቅም አላቸው በማለት የማንንም ጣልቃ ገብነት እንደማይፈልጉም አመልክተዋል።

አሜሪካ በሶማሊያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ይሄን ድርጊት ስትፈጽም የመጀመሪያዋ አይደለም።

አንዳንድ ተንታኞች “አሜሪካ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን ሕጋዊ መንግስት ለማስወገድ ካላት ከራስ ወዳድነት የመነጨ ፍላጎት ለዜጎች ግድያና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ስቃይ ተጠያቂ የሆነውን የአሸባሪውን የሕወሓት ቡድን እየደገፈች ነው” የሚል ክስ ይቀርባታል ብሏል ፕላስ ኒውስ በዘገባው።

አሜሪካ በሕዝብ ፍላጎት የተመረጠው መንግስት ጋር ሽብርተኝነት መዋጋትና የሽብር ቡድኖችን ድርጊት ማውገዝ ሲገባት ይሄን አለማድረጓ ገለልተኝነቷን ጥያቄ ወስጥ ከቶታል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በካደ መልኩ በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ችግር እየተባበሰ በመምጣቱ የአሜሪካ ዜጎች ኢትዮጵያን ለቀው ይውጡ በሚል ያወጣ የነበረው ተደጋጋሚ መግለጫ መጥፎ ነገር እንዲፈጠር ከመፈለግ የመነጨ ፍላጎት እንደሆነ በተንታንኞቹ ሲገለጽ መቆየቱን የኡጋንዳው ፕላስ ኒውስ የዜና ድረ ገጽ ባወጣው ዘገባ አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም