የኅብረተሰቡን ጤና የሚጎዳ አገልግሎት ሲሰጡ በተገኙ 35 ተቋማት ላይ እርምጃ ተወሰደ

84

ታህሳስ 19/2014/ኢዜአ /የኅብረተሰቡን ጤና በሚጎዳ መልኩ አገልግሎት ሲሰጡ በተገኙ 35 የምግብና መጠጥ አቅራቢ ተቋማት ላይ እርምጃ መውሰዱን የአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒት ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን አስታወቀ።


ባለስልጣኑ ከመጪው በዓልና ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶችን ከመቀበል ጋር ተያይዞ ሕገወጥ ተግባራት እንዳይፈጸሙ እያከናወናቸው ስለሚገኙ ተግባራት መግለጫ ሰጥቷል።

የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ትዕግስት በዳዳ እንዳሉት ባለስልጣኑ ምግብና መጠጥ አቅራቢ ድርጅቶች፣ ጤናና ጤና ነክ ተቋማትና የመድሃኒት ችርቻሮ ድርጅቶች ላይ የብቃት ማረጋገጫና የንፅህና አጠባበቅ ቁጥጥር ያደርጋል።

ተቋሙ በመደበኛነት ከሚያደርገው ቁጥጥር በተጨማሪ መጪዎቹን በዓላትና የሚመጡ እንግዶችን አቀባበል ታሳቢ በማድረግ በዘመቻ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘመቻው በተደረገ ቁጥጥርም የኅብረተሰቡን ጤና ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራትን የፈፀሙ 15 የምግብና መጠጥ አቅራቢ ተቋማት ሲታሸጉ 20 ተቋማት ደግሞ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

በዋናነት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ እንግዶች ሊያርፉባቸው የሚችሉ ተቋማት ላይ ያተኮረው ቁጥጥር እስከ መጪው ታህሣስ 26 እንደሚቀጥልም ጠቁመዋል።

በበዓላት ወቅት ምግቦችን ከባዕድ ነገር መቀላቀል እና ከሕገወጥ እርድ ጋር የተያየዙ ችግሮች ይከሰታሉ ያሉት ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ በእነዚህ ሕገወጥ ተግባራት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል።

አክለውም ኅብረተሰቡ ምርቶችን ሲገዛ ከባለስልጣኑ የብቃት ማረጋገጫ ያላቸው መሆናቸውን እንዲያረጋግጥ አሳስበዋል።

ሕገወጥ ተግባራት ሲያጋጥመውም በአቅራቢያው በሚገኙ የባለስልጣኑ ቅርንጫፎች እንዲሁም ለሕግ አስከባሪ አካላት ጥቆማ መስጠት እንደሚችል ገልጸዋል።

በተጨማሪም በነፃ የስልክ መስመር 8864 ጥቆማ ማድረስ እንደሚቻልም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም