ወደ አገር ቤት እየገቡ ለሚገኙ ዳያስፖራዎች ልዩ አቀባበልና መስተንግዶ እያደረገላቸው መሆኑን አየር መንገዱ ገለጸ

76

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ወደ አገር ቤት እንግባ ጥሪ ተቀብለው እየገቡ ለሚገኙ ዳያስፖራዎች ልዩ አቀባበልና መስተንግዶ እያደረገላቸው መሆኑን ገለጸ።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ወቅታዊ ፈተና በአሸናፊነት እንድትወጣ ዜጎች አንድ ላይ በመቆም ሀገርን ለማዳን እየተረባረቡ ይገኛሉ።

በተለይ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የቁርጥ ቀን ልጆች ለሀገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ጥብቅና አደባባይ በመውጣት አሳይተዋል።

በቃ ወይም NO MORE  በሚል የጀመሩት የአንዳንድ ምእራባውያንን ሴራ የመቃወም እንቅስቃሴም ዓለም የኢትዮጵያን እውነታ በሚገባ እንዲገነዘብ ከማስቻሉ ባለፈ መላ አፍሪካዊያንን በአንድ ጥላ ስር ማሰባሰብ ችሏል።  

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ወደ አገር ቤት እንግባ ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገራቸው እየገቡ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጥሪውን ተቀብለው የሚመጡ ዳያስፖራዎችን በልዩ ሁኔታ ለመቀበል ሁለት ኮሚቴ በማዋቀር እየሰራ መሆኑ ተገልጿል።

የአየር መንገዱ የግራውንድ ሰርቪስስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ታደለ ባረጋ ለኢዜአ እንደገለጹት፣ ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገር እየገቡ ለሚገኙ ዳያስፖራዎች ልዩ አቀባበልና መስተንግዶ እየተደረገላቸው ነው።

የተቋቋሙት ኮሚቴዎችም የደህንነትና የጸጥታ ጉዳዮችን የሚከታተሉና ወደ ሀገር ቤት ለመጡ ወገኖች የሚሰጠውን አገልግሎት በትኩረት የሚከታተሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ዳያስፖራዎቹ ችግር እንዳያጋጥማቸው ካጋጠማቸውም ኮሚቴው ወዲያው ተነጋግሮ እርምት በመውሰድ የተሳለጠ አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

ጥሪውን ተቀብለው ወደ ሀገራቸው የሚመጡ ዳያስፖራዎች ቆይታቸውን አጠናቀው ወደሚኖሩበት ሀገር ሲመለሱ አገልግሎቱ በተመሳሳይ ሁኔታ ያለ እንከን እንደሚቀርብላቸው አንስተዋል።

አየር መንገዱ ከእነዚህ ዝግጅቶች በተጨማሪም ዳያስፖራው በረዥም ጊዜያት ሀገሩን ናፍቆ ሲመጣ ደስ እንዲለው በሚል እሳቤ የኢትዮጵያ መገለጫ የሆነውን የቡና ስነ-ስርዓት በመነሻቸውና በመዳረሻቸው ማዘጋጀቱን ገልጸዋል።

አገልግሎቱን እያገኙ ካሉት ዳያስፖራዎች ጥሩ ምላሽ እየተገኘ መሆኑንም ዳይሬክተሩ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም