በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲረጋገጥ አሜሪካ ፖሊሲዋን ልታርም ይገባል

101

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እየተደረገ ያለው ጥረት እንዲሳካ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ኢትዮጵያን አስመልክቶ የሚከተለውን አካሄድ ሊያርም እንደሚገባው ምሁራን ገለጹ።

አሜሪካዊቷ ምሁር ብሮንዊን ብሩተን እና ካናዳዊቷ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ በፎሬይን ፖሊሲ ድረ-ገጽ ባስነበቡት ጽሁፍ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፖሊሲ ዳግም ልታጤነው ይገባል ብለዋል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ የምትከተለው ፖሊሲ በብዙ መልኩ ተቀባይነት እያጣ መሆኑንም ምሁራኑ ማሳያዎችን ዋቢ አድረገው አስረድተዋል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጥምር ጦር ተመትቶ ከአፋርና ከአማራ ክልሎች እንዲወጣ የተደረገው አሸባሪው ህወሓት ከወረራቸው አካባቢዎች እንዲወጣ አሜሪካ ግፊት አለማድረጓ ፖሊሲዋ የተሳሳተ መሆኑን ያሳያል ብለዋል።

ለዓመታት በህወሓት የሚመራው የኢትዮጵያን መንግሥትን ያለ አንዳች ሃፍረት የአፍሪካ ቀንድ “የመረጋጋት መስህብ” በማለት ስታወድሰውና የገንዘብ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷ ስህተት እንደነበር አስምረውበታል። 

አሜሪካ በአፍሪካ የነበራት ተደማጭነትና ተሳትፎ እያነሰ እንደ ቻይና፣ ሩስያ፣ ቱርክና የባህረ ሰላጤው አገራት እየተተካ መምጣቱን ገልጸው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ ለፕሬዝዳንት ባይደን መልካም አጋጠሚ አይሆንም ብለዋል።

የባይደን አስተዳደር አካሄዱን ካላስተካከለ በቀጣናው ለሚፈጠረው ማንኛውም ፖለቲካዊ ክስተት አገራቸው ምንም ዓይነት ድምጽ ሊኖራት እንደማይቸል አስጠንቅቀዋል።

በአሁኑ ወቅት አሜሪካ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም እንዲፈጠር አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችልበት መልካም ዕድል መፈጠሩንም ምሁራኑ ጠቁመዋል።

ምሁራኑ አክለውም ዋሽንግትን ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ያላትን አዛኝነት በማለዘብ ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲ የምታደርገውን ሽግግር መቀበል ይኖርባታል ብለዋል።

አሜሪካ ለሽብር ቡድኑ በግድ የለሽነት ታደርግ በነበረው ከፍተኛ የገንዘብና ፖለቲካዊ ድጋፍ  ምክንያት ቡድኑ ወደ ግጭት መግባቱን ማጤን እንዳለባት አስገንዝበዋል።

የባይደን አስተዳደር አሸባሪው ህወሓት ታሪካዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ ባልሆነ መንገድ የሚያደርገውን የመሬት ወረራ ተጽዕኖ እና የማይገባውን የመጠየቅ አባዜን ጨምሮ ስለ ኢትዮጵያ ውስጣዊ የፖለቲካ ምህዳር በቂ ግንዛቤን መያዝ እንደሚገባውም ግልጽ አድርገዋል።

የአፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” ብሎ ከሰየመው ቡድን ጋር መንግሥት እንዲደራደር ጫና መፍጠርም የኢትዮጵያን ልዓላዊነትና የግዛት አንድነት የሚፃረር በመሆኑ ተገቢነት እንደሌለው አስምረውበታል።

ጦርነቱ እንዲቋጭ ለዋሽንግተን የተሻለው መንገድ የሚሆነው ግጭቱን የጠነሰሱት የአሸባሪው ህወሓት መሪዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ ማቅረብ እንደሆነም ግልጽ አድርገዋል።

የህወሓት መሪዎች ለሰላም ሲሉ እጃቸውን ለመስጠት ፈቃደኛ ካልሆኑ ግን አሜሪካ ማዕቀብ ልትጥልባቸው ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም