በኢትዮጵያ ከ10 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት ወስደዋል

53

አዳማ ፤ ታህሳስ 19/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ እስካሁን ከ10 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚበልጡ ዜጎች የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያግዝ ክትባት መውሰዳቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የኮቪድ -19 በሽታ መከላከያ ክትባትና የመደበኛ ክትባት አፈጻጸም የግምገማ መድረክ  በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ  ዱጉማ፤ በሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስ በከፋ ደረጃ እየተስፋፋ መሆኑን ሁላችንም ማወቅ አለብን ብለዋል በመድረኩ ላይ ባደረጉት ንግግር።

ይህም የጥንቃቄ ጉድለትና ለመከላከል  የወጡ መመሪያዎች በሁሉም ቦታዎች ተፈፃሚ ያለመሆኑ ጠቅሰዋል።

የመከላከል ስራ ላይ ርብርብ ቢደረግም ማህበረሰቡ ዘንድ ክትባቱን በአግባቡ ያለመውሰድ ሌላው ትልቅ ችግር እንደሆነ ያመለከቱት ዶክተር ደረጀ፤ ይህም ሆኖ እስካሁን በሀገሪቱ  ከ10 ነጥብ 9 ሚሊዮን የሚበልጡ  ዜጎች ክትባቱን መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

ከእነዚህ ውስጥ ከ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የተከተቡት በዘመቻ መሆኑን አስረድተዋል።

ዕድሜያቸው ከ12 ዓመት በላይ ለሆኑ ልጆች ጭምር ክትባት መውሰዳቸውን ጠቅሰው፤ አሁንም ከጤና ሴክተር ሙያተኞችና አመራሮች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ተገቢውን ትኩረት በመስጠት  የበሽታ ስርጭት መግታት ላይ መረባረብ አለብን ነው ያሉት።

በቀጣይነት ተመሳሳይ ዘመቻዎች እንደሚኖሩና የክትባት አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን የሚያስችል ጠንካራ የአሰራር ስርዓት ከፌዴራል እስከ ክልሎች ድረስ መዘርጋቱንም አመልክተዋል።

በሽታውን ለመከላከል መገናኛ ብዙሃን፣ የሃይማኖት መሪዎች፣አባ ገዳዎች፣የሀገር ሽማግሌዎችና የፖለቲካ አመራሩ የሚጠበቅብንን ሚናና ሀገራዊ ሃላፊነት መወጣት አለብን  ሲሉም ዶክተር ደረጀ አሳስበዋል።

አጋር ተቋማት በፋይናንስ በመደገፍ፣ በአቅም ግንባታና ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ ክትባቱ ወደ ሀገር እንዲገባ ከማድረግ ባለፈ በዜጎች ዘንድ ተደራሽ እንዲሆን ላደረጉት አስተዋጽኦ ምስጋና አቅርበዋል።

በሚኒስቴሩ የእናቶችና ህፃናት ጤና ዘርፍ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው፤ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በማህበረሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው  ክትባቱን ያለመቀበል አመለካከት ተገቢ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

በቀጣይ በአሸባሪው ቡድን ጉዳት በደረሰባቸው የሀገራችን የሰሜኑ ክፍል ጭምር በዘመቻም ሆነ በመደበኛነት ክትባቱ እንዲደርስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በጦርነቱ የተጎዱ አካባቢዎችን በክትባት ለመድረስ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

ከዛሬ ጀምሮ ለአራት ቀናት በሚቆየው መድረክ ከሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የጤና ሴክተር የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው::

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም