ተፈናቃይ ወገኖችን መልሶ በማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን በመገንባት የበኩላችንን እንወጣለን

56

ታህሳስ 19/2014/ኢዜአ /የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋምና የወደሙ መሰረተ ልማቶችና ተቋማትን በመገንባት የበኩላቸውን እንደሚወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

አሻባሪዎቹ ህወሓትና ሸኔ በፈጸሙት ወረራና ጥቃት በርካታ ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ፣ የግልና የመንግስት ንብረትና መሰረተ ልማቶች ወድመዋል።

በከፍተኛ ደረጃ የጉዳቱ ሰለባ ከሆኑ አካባቢዎች መካከል ምስራቅ አማራና የአፋር ክልል አካባቢዎች ተጠቃሽ ናቸው።

በእነዚህ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን የማቋቋምና የወደሙ ተቋማትን መልሶ የመገንባት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችም በዚህ የመልሶ ማቋቋምና ግንባታ ሂደት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት /መኢአድ/ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሉጌታ አበበ፤ ፓርቲያቸው ሀገር በማዳን ዘመቻው በንቃት መሳተፉን ተናግረዋል።

በዚህም አባላቱና አመራሩ ከወገን ሃይል ጎን በመሰለፍ ግንባር ድረስ በመሄድ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል ብለዋል።

ፓርቲው አሁን በሚካሄደው የመልሶ ግንባታም በተሻለ መልኩ ለመንቀሳቀስ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

አሻባሪው ህወሓት በፈጸመው ኢ-ሠብዓዊ ድርጊት ከህጻን እስከ አዛውንት ለስነ-ልቦና ችግር ተዳርገዋል ያሉት አቶ ሙሉጌታ ይህን ችግር ለማቃለል ከስነ-ልቦና ባለሙያዎችና ከሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ጋር በመሆን የስነ-ልቦና ግንባታ ስራ ለመስራት እየተንቀሳቀስን ነው ብለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ከአዲስ አበባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጋር በመሆን በአፋር ክልል አንድ፣ በአማራ ክልልም እንዲሁ አንድ ተቋም ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም የዘማች ቤተሰቦችን በተለያየ መልኩ ለማገዝ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ /ኢዜማ/ ዋና ጸሃፊ አቶ አበበ አካሉ፤ ፓርቲው በህልውና ዘመቻ ወቅት በተለያየ መልኩ ሲንቀሳቀስ መቆየቱን ተናግረዋል።

እስካሁንም 250 ሺህ ብር እና አራት ሚሊዮን ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ለተፈናቀሉ ወገኖች ማድረጉን ገልጸዋል።

ፓርቲያቸው በሚካሄደው የመልሶ ግንባታ ስራም የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አሳውቀዋል።

ፓርቲያችን ከሌሎች ጋር በመሆን የበኩሉን ለመወጣት እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት ድርጅት ተወካይ አቶ ዘርይሁን ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

በተለይም በጤና እና በትምህርት ተቋማት ላይ የደረሰውን ውድመት ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም