የአሸባሪው ህወሓት ወራሪ ቤቴንና ጥሪቶቼን በማቃጠል የ10 ቤተሰቤን መጠለያ አሳጥቶኛል

71

አዲስ አበባ ታህሳስ 19/2014(ኢዜአ) የህወሓት የሽብር ቡድን ወራሪዎች መኖሪያ ቤታቸውን እና በውስጡ የነበሩ ጥሪቶቻቸውን በማውደም 10 የቤተሰብ አባላትን መጠለያና የዕለት ጉርስ እንዳሳጧቸው አርሶ አደር ማሞ አሰፌ ተናገሩ።

አርሶ አደር ማሞ አሰፌ ውልደት እና እድገታቸው በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ በራማ ቀበሌ 09 የቀዩ ጋሪያ ታዳጊ ከተማ ነው።

መተዳደሪያቸው እርሻ ሲሆን በስደት በዓረቡ ዓለም ከሚኖሩ ሁለት ልጆቻቸው ድጋፍ በአንድ ሚሊዮን ብር ወጪ መኖሪያ ቤት ገንብተው እንደነበር ይናገራሉ።

ነገር ግን የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች በቤታቸው ውስጥ ለአዲስ ዓመት ክብረ በዓል የተጠመቀ ጠላ አውጥተው ከጠጡ በኋላ መኖሪያ ቤታቸውን እንዳቃጠሉባቸው ነው የገለጹት።

የአካባቢው ነዋሪዎች ወራሪው ቡድኑ ያስነሳውን እሳት ለማጥፋት ቢማጸኗቸውም ዙሪያውን ከበው በመከልከል ሙሉ ለሙሉ እስኪወድም ድረስ በስፍራው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

የአካባቢው ነዋሪ እሳቱን እናጥፋ ቢልም 'እኛን የተዋጋ ሰው ነው ብናገኘው በመኪና እየጎተትን መቀሌ ነበር የምንወስደው' በማለት አንድ ሚሊዮን ብር ያወጣሁበትን፣ የ10 ቤተሰብ መጠለያ ቤቴን አውድመውታል ሲሉ በቁጭት ገልጸዋል።

በአሸባሪው ወራሪ በእሳት በጋየው መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ 200 ሺህ ብር የሚገመቱ ሶፋ፣ 3 ሞዝቮልድ አልጋ፣ 4 ቁም ሳጥን፣ ቡፌ፣ 20 ኩንታል ጤፍ እና 10 ኩንታል ማሽላ አብሮ ወድሟል ብለዋል።

እንደ አርሶ አደር ማሞ ገለጻ የሽብር ቡድኑ ወራሪዎች ቤት ንብረታቸውን ያወደሙባቸው ተዋግተኸናል፣ የብልጽግና ፓርቲን ትደግፋለህ በሚል ምክንያት ነው።

የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ይመር ነጋሽ የሚቃጠለውን ቤት ለመታደግ ለወራሪዎቹ ጥያቄ ቢያቀርቡም ከልክለዋቸው ንብረቱ ሙሉ ለሙሉ እስከሚወድም ይጠብቁ እንደነበር ተናግረዋል።

የአርሶ አደር ማሞ አሰፌ ቤት እና በውስጡ የነበሩ ንብረቶቹ ሙሉ በሙሉ በሽብር ቡድኑ ወራሪዎች ወድሞ የቤተሰቡ አባላት ያለ ምንም መጠለያ ሜዳ ላይ መቅረታቸውንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም