በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ተመረቀ

104

ታህሳስ 19/2014/ኢዜአ/ ማራቶን ሞተርስ ኢንጅነሪንግ በኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ገንብቶ ለአገልግሎት ዝግጁ አድርጓል።

የኤሌክትሪክ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያው ተሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ ቻርጅ  እስከ 300 ኪሎ ሜትር ድረስ መጓዝ የሚያስችላቸው እንደሆነ ተገልጿል።

አገር በቀል ኩባንያው ማራቶን ሞተርስ በ2012 ዓ.ም በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገጣጠመውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ማስመረቁ ይታወቃል።

ኩባንያው በዛሬው ዕለትም በአገሪቷ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ መሙያ ጣቢያ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች በተገኙበት አስመርቋል።

ድርጅቱ በተጨማሪም በኢትዮጵያ የተገጣጠመውን "ሃንዳይ ኮና" የተሰኘ ሁለተኛውን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሞዴል ለምረቃ አብቅቷል።

ኩባንያው ታዳሽ ሀይልን ከማስፋትና የአካባቢ ብክለትን ከመቀነስ አንፃር አስተዋፅኦ ያበረክታሉ የተባሉትን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚነት ለማስፋት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ፤ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታዋ ለመመለስ የተጀመረው ትግል በሁሉም መስክ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።

የግሉ ዘርፍ ተዋንያን በአገር ግንባታ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ ለማጠናከር መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የንግድ ሚኒስትር መላኩ አለበል በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላይ ከሚደረጉ ጫናዎች አንዱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዲከሰት ማድረግ በመሆኑ የተመረቀው ጣቢያ ይህን ለመቋቋም ያስችላል ብለዋል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ ደግሞ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያውና ተሽከርካሪዎቹ የውጭ ምንዛሬን በመቀነስ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ።

በተለይም ኢትዮጵያ ነዳጅ ከውጭ ለማስገባት የምታወጣውን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ በአገር ውስጥ እንዲቀር በማድረግ ለኢኮኖሚው አበርክቶ ይኖረዋል ነው ያሉት።

የድርጅቱ መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ መልካሙ አሰፋ ፕሮጀክቱ የውጭ ምንዛሬ ከማዳን ባሻገር ኢትዮጵያ በሃይድሮ ኤሌክትሪክ ታዳሽ ሀይል ያላትን እምቅ አቅም ለመጠቀም ያግዛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም