የኮቪድ19 ወረርሺኝን በመከላከል ረገድ የታየው ቸልተኝነት ዋጋ እያስከፈለ ነው

45

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ)የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከል ረገድ የታየው ቸልተኝነት እና መዘናጋት ዋጋ እያስከፈለ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት እና የመደበኛ ክትባት አፈጻፀም ግምገማ ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ከመጡ የጤና ቢሮ ሀላፊዎች፣ ከህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ሀላፊዎች፣ ከአጋር አካላትና በኮቪድ 19 በሽታ መከላከያ ክትባት ዙሪያ እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎች በተገኙበት በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በዚሁ የግምገማ መድረክ የጤና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ እንደተናገሩት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመግታት እና ለመቆጣጠር የጤና ሚኒስቴር ከፍተኛ ግብአት በመመደብ ላለፉት ሁለት አመታት ሲሰራ እንደነበርና የመከላከያ ክትባቱንም አስር ሚሊየን ለሚጠጉ ሰዎች ማዳረስ መቻሉን ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ለኮቪድ 19 ወረርሽኝ የሚመከሩ መከላከያ መንገዶችን ችላ በማለቱ እና ከፍተኛ መዘናጋት ውስጥ በመግባቱ በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መምጣቱን አስረድተዋል።

ይህም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ህብረተሰቡ በኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት ዙሪያ ግንዛቤውን እንዲያሳድግና ክትባቱን ጨምሮ ሌሎች የጥንቃቄ መንገዶችን እንዲያከብር ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ዳይሬክተር ዶ/ር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወደ ሀገራችን ከገባ ጀምሮ በጤና ተቋም በተገኘ መረጃ ብቻ ስድስት ሺ ስምንት መቶ የሚሆኑ ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን እና በርካታ ዜጎችም ለጤና፣ ለማህበራዊ እና ለኢኮኖሚያዊ ችግሮች መዳረጋቸውን አንስተዋል።

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከላከያ ክትባትን እና ሌሎች መከላከያ ምክሮችን ዜጎች ካለመዘናጋት እንዲጠቀሙ ሁሉም ባለድርሻ አካላት እስካሁን ሲያደርጉት የነበረውን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

ሌሎች የመደበኛ ክትባቶችም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ቢኮንም እንኳን ጥሩ አፈጻጸም እንዳለው አንስተው በተለይ የግጭት አካባቢ በነበሩ ስፍራዎች ትልቅ ስራ እንደሚጠይቅ እና በዚህ ዙሪያም በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የግምገማ መድረኩ ለተከታታይ አራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች እንደሚለይበት እና ለቀጣይ ስራ ግብአት የሚገኝበት እንደሆነም ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም