የአማራ ክልልን ባህላዊ እሴቶች ጠብቆ ለትውልድ ለማስተላለፍ የድርሻችንን እንወጣለን---አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

105
ባህርዳር ነሃሴ 20/2010 የአማራ ህዝብ ከትውልድ ትውልድ እያስተላለፈ ያቆየንን የባህል እሴቶች በማልማት ለሃገር እድገት ለመጠቀም የበኩላችንን እንወጣለን ሲሉ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ። “የሻደይ፣አሸንድዬና ሶለል በዓል ለሀገራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በባህርዳር ከተማ የበዓሉ ማጠናቀቂያ ተካሂዷል። በበዓሉ ላይ ርዕሰ-መስተዳደሩ እንደገለጹት የአማራ ህዝብ ለሃገራችን ድንበርና ለሉአላዊነት መከበር ቀዳሚ ሚና ሲጫወት መኖሩን ተናግረዋል። የበርካታ ባህላዊና፣ኪነጥበባዊ እሴቶች መፍለቂያ መሆኑን የሻዴይ፣አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች ጨዋታ ለብዙ ሺህ ዓመታት ጠብቆ ማቆየቱ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል። በሰሜን ወሎና ዋግህምራ ሲከበር የኖረውን የልጃገረዶች በዓል በክልል ደረጃ ያከበርነው ለዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ያለንን ድርሻ ለመወጣት ነው ብለዋል። የበዓሉን ትውፊትና እሴት ጠብቆ ለትውልድ ማስተላለፍ ታሪካዊ አደራ በመሆኑ የክልሉ መንግስት የሚጠበቅበትን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል። የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ወይዘሮ ፎዚያ አሚን በበኩላቸው የሻደይ፣አሸንድዬና ሶለል የልጃገረዶች በዓል የመተሳሰብ፣የመፈቃቀርና የመደመር ተምሳሌት ነው ብለዋል። ይህንን አኩሪ እሴት በማልማትና በማስተዋወቅ ሃገራዊ ሃብት አድርጎ ለዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ መስሪያ ቤታቸው እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል። “ባህላዊ ጨዋታው በየዓመቱ ከነሐሴ 16 ጀምሮ ለአንድ ሳምንት የሚከበር ነው” ያሉት ደግሞ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሂሩት ካሳው ናቸው። በዓሉ የሴቶች የዘመናት ነጻነት ተምሳሌት ሆኖ የኖረ እንደሆነ ኃላፊዋ አስረድተዋል። “በዓሉ በሃገራችንና በዓለም ደረጃ ቢስፋፋ ለሰላም፣ለነጻነትና እኩልነት መስፈን አስተዋጽኦው የጎላ ነው” ብለዋል። በዓሉ በባህርዳር ከተማ በሚሊኒየም አደባባይ ዛሬ ሲከበር ከበዓሉ ባለቤት ልጃገረዶች በተጨማሪ የክልሉና የፌዴራል ከፍተኛ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም