እንግዶች ሰላማቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል-ፖሊስ

108

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) እንግዶች ሰላማቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቀ፡፡

ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ዳያስፖራዎች እና ሌሎች እንግዶች ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን በሆቴል እና በመዝናኛ ሥፍራ ላይ ከተሰማሩ የተቋማት ሃላፊዎች እና የጥበቃ ባለሙያዎች ጋር ውይይት ተካሂዷል፡፡

ምክትል ኮሚሽነር መንገሻ ሞላ በውይይቱ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፥ ውድቀታችንን የሚመኙ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ዛሬም ሆነ ወደ ፊትም አርፈው እንደማይተኙ አንስተዋል፡፡

የአገራችንን መልካም ገጽታ ለአለም ለማሳየት የሚመጡ እንግዶች ሰላማቸውና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆን ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ነው የተናገሩት፡፡

በጉዳዩ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት ኮማንደር ሰለሞን ፋንታሁን በበኩላቸው፥ በሆቴሎች እና መዝናኛ ስፍራዎች አካባቢ የሚታዩ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ የመፍትሄ ሃሳቦችን አመላክተዋል፡፡

የእንግዶችን ደህንነት በማስጠበቅ ነጻነት እንዲሰማቸው ማድረግ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ትኩረት መስጠት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎችም የሚመጡ እንግዶችን ደህንንታቸው በተጠበቀ መልኩ አገልግሎት ለመስጠት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የተሻሉ የጥበቃ ባለሙያዎች መመደባቸውን ገልጸዋል፡፡

የጥበቃ ሥራው በደህንነት ካሜራዎች ጭምር የታገዘ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

በመድረኩ በመረጃ ልውውጥ፣ በስልጠናና ተዛማጅ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎች በሃላፊዎቹ ምላሽ የተሰጠባቸው መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም