ኢትዮጵያ የገጠማት ተግዳሮት ፈታኝ ቢሆንም ታግሎ በማለፍ ዳግም የአፍሪካዊያን ኩራት የምትሆንበትን እድል ይፈጥራል

69

ታህሳስ 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የገጠማት ተግዳሮት ፈታኝ ቢሆንም በፅናት ታግሎ በማለፍ ዳግም የአፍሪካዊያን ኩራት የምትሆንበትን እድል ይፋጥራል ሲሉ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ ከተለያዩ ሀገራት በቅርቡ ወደ ሀገር ቤት ለመጡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ሰራዊት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ትናንት ምሽት በሀዋሳ ኃይሌ ሪዞርት የእራት ግብዣ አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት፤ የቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት ለሀገራቸው ክብርና አንድነት ሲሉ በየግንባሩ ተዋድቀዋል።

ሆኖም ከፋፋይና ኢትዮጵያ ጠል በሆነው በአሸባሪው የህወሓት ሥርዓት ተገፍተው ከሚወዷት እናት ሀገራቸው ለመውጣት መገደዳቸውን አስታውስዋል።

ይሁንና ዛሬም ሀገሪቱ የህልውና አደጋ በተጋረጠባት ወቅት ለእናት ሀገራችን እስከ ሕይወት መስዋዕትነት እንክፍላለን ብለው ወደ ሀገር ቤት በመምጣት ዳግም የቁርጥ ቀን ልጆች መሆናቸውን አስመስክረዋል ብለዋል።

ዛሬ በአጋጣሚ ህዝብ የማስተዳደር ኃላፊነት ላይ ብንሆንም ለሀገር ክብርና ነፃነት እስከምን ድረስ መስዋዕትነት መክፈል እንደሚገባን ከእናንተ እንማራለን ነው ያሉት።

ኢትዮጵያውያን ጥንትም የጥቁር ህዝቦች የነፃነት ቀንዲል ነን ያሉት አቶ ርስቱ ፤ አሁን የገጠመን የህልውና አደጋ ምንም እንኳ ፈታኝ ቢሆንም በፅናት ታግሎ በማለፍ ዳግም የአፍሪካዊያን ኩራት መሆን የሚቻልበት እድል እንደሚፈጥር አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ ፈተና በገጠማት ወቅት በተለይ በተስፋፊው የሲያድባሬ መንግስት ወረራን ለማክሸፍ በጦርነቱ መሳተፋቸው ያስታወሱት የቀድሞ የአየር ኃይል አባል ኮሎኔል ክንፋ ሀብተወልድ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሓትና ጋላቢዎቹ በሚነዙት የሀሰት ፕሮፖጋንዳ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች፣ ተሸንፋለች የሚል ውዥንብር ከሀገር ውጭ ሆኖ መስማት እጅግ የሚያም እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ለእናት ሀገራችን የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ኢትዮጵያ ወይም ሞት በማለት መጥተናል ሲሉም ገልጸዋል።

ወደ ሀገር ከመጡ በኋላ የተመለከቷት ኢትዮጵያ አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራትና ሚዲያዎቻቸው ከሚነዙት በእጅጉ የተለየና ፍጹም ሠላማዊ ድባብ እንዳለ ማረጋጋጥ እንዳቻሉ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት ለመኮንኖቹ የደቡብ ክልል ብሔር ብሔረሰቦችን የሚገልፁ የተለያዩ የባህል አልባሳት በስጦታ አበርክቶላቸዋል።

በመርሀ-ግብሩ ላይ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ እና ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም