ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

109
ነሃሴ 20/2010 የብሄረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ነሃሴ 17 እና 18 ቀን 2010 ዓ.ም ለሁለት ቀናት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ በብአዴን 12ኛ መደበኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ረቂቅ ሪፖርትና ለጉባዔው በሚቀርቡ ሌሎች ወቅታዊና መደበኛ ጉዳዮች ላይ ተወያቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡ የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በህዝቡ ሁለንተናዊ ተሳትፎና ባለቤትነት በሀገር ደረጃና ብአዴን በሚመራው የአማራ ክልል የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝና ታሪካዊ ጊዜ ላይ የሚካሄድ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ድርጅቱ የመሪነት ሚናውን ከምንጊዜውም በላይ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችሉ አቅጣጫዎችና ውሳኔዎች ለጉባኤው እንዲቀርቡ ጥልቀት ያለው ውይይት ካካሄደ በኋላ በጉባዔ አጀንዳዎችና በሌሎች ጉዳዮች ስምምነት ላይ በመድረስ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡ 1) በመቀጣጠል ላይ ያለውን ክልላዊና ሃገራዊ ለውጥ ለመጠበቅ፣ መሰረቱን ለማስፋትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ እንዲቻል ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሕጋዊ የለውጥ እርምጃዎች በተከታታይ ይወሰዳሉ፡፡ በዚህ ሂደት ብአዴን የደረስንበት መድረክ የሚጠይቀውን ደረጃ ያሟላ ተመራጭ የፖለቲካ ድርጅት ሆኖ በመገኘት የክልሉን፤ ብሎም የሃገራችንን ህዝብ የዲሞክራሲና የልማት ጥያቄዎች ከፍ ባለ ደረጃና በዘላቂነት እየመለሰ ግንባር ቀደም አታጋይ ድርጅት ለመሆን ቆርጦ የተነሳ መሆኑን ለመላው የአማራ ህዝብ፣ ለድርጅቱ አባላትና አመራሩ በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ያበስራል፡፡ 2) የአማራን ህዝብ ታሪክ፣ ትግል፣ ባህል እና ስነ ልቦና በአግባቡ የተገነዘበና የተረዳ፣ እንዲሁም አሁን ከተፈጠረው አዳጊ ሀገራዊና ክልላዊ ሁኔታ ጋር አብሮ የሚራመድ የፖለቲካ ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ እንዲኖር ማድረግ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ድርጅቱ ቀደም ሲል ሲመራበት የነበረው ፕሮግራምና መተዳደሪያ ደንብ የህዝቡንና የአባላቱን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ግለጽ በሆነ ተሳትፎ እንዲሻሻል ይደረጋል፡፡ በዚህ ረገድ የጉዳዩ ባለቤት የሆኑት የድርጅታችን አባላት ጥያቄ እስከሆነ ድረስ የድርጅቱን ስያሜ ጨምሮ ሌሎች ፖለቲካዊ ጉዳዮችም በአግባቡ እየተፈተሹ ሥርዓቱን በጠበቀ መንገድ ማሻሻያ ሊደረግባቸው እንደሚችል ማዕከላዊ ኮሚቴው ያምናል፡፡ 3) የአማራ ብሄርተኝነት በህብረ-ብሄራዊነትና በዲሞክራሲያዊ የኢትዮጵያ አንድነት መርህ ለይ ተመስርቶ እንዲገነባ ብአዴን በጽናት ይታገላል፡፡ በፌዴራል ሥርዓቱ ውስጥ የህዝቦች እራስን በራስ የማስተዳደር፣ የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነጻነት የመስራትና የመኖር መብቶች ሁሉ በትክክለኛው ገጽታና በተሟላ መንገድ እንዲከበሩና ኢትዮጵያ ለሁላችንም የተመቸች ሃገር እንድትሆን ብአዴን ከሌሎች እህት ድርጅቶችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በጋራ በመሆን ይሰራል፡፡ ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ መንግስት አባላት የሆኑ ክልሎች አከላለል በህዝቦች እውነተኛ ፍላጎትና ንቁ ተሳትፎ፣ ብዝሃነትንና ሃገራዊ አንድነትን በሚያጠናክር አግባብ ሕገ መንግስቱን መሰረት አድርጎ እንዲከለል እንታገላለን፡፡ ባለፉት የትግል ዓመታት ክልላችንን ጨምሮ በመላ ኢትዮጵያ ለህዝቦች መፈናቀልና መሰደድ፣ ለህይወት መጥፋትና ንበረት መውደም ምክንያት የሆኑ የወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቷቸው በህዝብ ነጻ ተሳትፎ እንዲፈቱ ብአዴን በምክንያት ለይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ትግል ያካሂዳል፡፡ 4) የሃገሪቱም ሆነ የክልሉ ሕግጋተ መንግሥታት ዘመናዊ፣ ዓለም ዓቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችንና መሰረታዊ የዴሞክራሲ መብቶችን አሟልተው የያዙ፣ የዜጎች የቃል ኪዳን ሰነድ እንደመሆናቸው መጠን ለህገ መንግሰታዊ መብቶች መከበር ብአዴን በጽናት ይታገላል፡፡ ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ማሻሻያ ሳይደረግበቸው የዘለቁት ህገ መንግስታዊ ድንጋጌዎቻችን ውስጥ አንዳንዶቹ አገራችን ዛሬ ከደረሰችበት የዴሞክራሲ እድገት ደረጃ ጋር ተጣጥመው መሄድ አለባቸው የሚለውን የህዝብ አስተያየትና ጥያቄ ብአዴን በበጎ ጎኑ ይመለከተዋል፡፡ ስለሆነም እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ሕገ መንግስቱ ራሱ ያስቀመጠውን ሥርዓት ጠብቀው እስከቀረቡ ድረስ የሚነቀፉበት ምክንያት የለምና ሕጋዊና ትክክለኛ ምላሽ አግኝተው በሃገራችን የተጀመረው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የበለጠ እንዲጠናከር ብአዴን በቁርጠኝነት ይሰራል፡፡ 5) የህግ የበላይነት መከበር ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ወሳኝ እንደሆነ ብአዴን በጽናት ያምናል፡፡ እስካሁን በተካሄደው ትግል በዜጎች ለይ የተፈጸመን ማንኛውንም ኃላፊነት የጎደለው ኢ-ሕገ መንግስታዊ ተግባር እያወገዝን በእንዲህ አይነት ድርጊት ውስጥ ገብቶ የተገኘ ማንኛውም ቡድን፣ የመንግስት ባለስልጣንና ግለሰብ የሃገሪቱ ህግ በሚፈቅደው አኳኋን ለህግ ቀርቦ ተጠያቂ እንዲሆን በጽናት እንታገላለን፡፡ ከዚህም በኋላ በሃገራችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሟላ መንገድ እንዲከበሩ፣ ዜጎች በገዛ ሃገራቸው ተዋርደው ሊኖሩ እንደማይገባ፣ በዚህ ረገድ የሚፈጸምን ማነኛውንም ኢ-ሕገ መንግስታዊ ድርጊትም ውጉዝ እንደሆነ ብአዴን አጥብቆ ያምናል፡፡ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ፈር ለማሳት የሚፈጸም ማንኛውንም ሕገ ወጥ ተግባር በመታገል በሃገራችንና በክልላችን ዋስትና ያለው ዴሞክረሲ እንዲገነባ ይደረጋል፡፡ 6) የግለሰብና የቡድን መብቶች ተጣጥመው መከበር እንዳለበቸው እናምናለን፡፡ የግለሰብ መብት ባልተከበረበት የቡድን መብት ቦታ እንደማይኖረው፣ የቡድን መብት ባልተከበረበትም የተሟላ ዴሞክራሲ እንደማይኖር የታወቀ ነው፡፡ ሁለቱን መብቶች አጣጥሞ በመሄድ ረገድ ሕገ መንግስታችን ብዙ እርቀት ተጉዟል፡፡ በመሆኑም በሃገራችን ትክከለኛ ዴሞክራሲ እንዲገነባ ትልቅ መሰረት ተጥሏል፡፡ ይሁን እንጅ ባለፉት ዓመታት በሁሉም መስክ በቂ ሥራ ካለመሠራቱም በላይ በተለይ ደግሞ ለቡድን መብት መከበር የተሰጠውን ትኩረት ያክል ለግለሰብ መብትም ስላልተሰጠ የተጀመረው የቡድን መብት የማስከበር ሥራ ወደፊት ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ትኩረት ተነፍጎት የቆየው የግለሰብ መብት በሚዛናዊነት የሚከበርበት ሥርዓት እውን እንዲሆን ይደረጋል፡፡ 7) ብአዴን በውስጡ ጤናማ የሆነ የአመራር ቅብብሎሽ ሥርዓት ይኖር ዘንድ ለአመራር ግንባታ ሥራ በቂ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል፡፡ በተለይም አሁን እየታየ ያለውን ከፍተኛ የፖለቲካ ንቃትና ምርጥ ህዝባዊ ማዕበል በእድልነት በመጠቀም በድርጅቱ ውስጥ በብቃት የተገነባ ብልህ፣ አርቆ አሳቢና አስተዋይ ተኪ አመራር እንዲኖር የተማረውን ወጣት ማዕከል ያደረገ የአመራር ምልመላና ግንባታ ስራ ያካሂዳል፡፡ በአንጻሩም አሁን ከተደረሰበት የትግል መድረክና ከለውጡ እንቅስቃሴ ጋር አብረው መጓዝ በተሳናቸውና ህዝባዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት መወጣት ባልቻሉ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ለይ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን ድርጅቱ ራሱን የማጥራት እንቅስቃሴውን አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡ የብአዴን 12ኛ ድርጅታዊ ጉባኤም ይህንኑ ግምት ውስጥ ያስገባ ውሳኔ የሚተላለፍበት እንዲሆን በዚህ አጋጣሚ ለመላ አባላችንና አመራራችን ጥሪ እናቀርባለን፡፡ 8) ሁለተኛው የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን እቅድ በብቃት እንዲመራና በቀሪ ጊዚያት በሚሰራ ስራ ያለፈውንም ማካካስ በሚችልበት ደረጃ ለይ እንዲደርስ ህዝቡን፣ ወጣቶችን፣ ባለሃብቱንና ምሁራንን በማረባረብ ክልላዊና ሃገራዊ እድገት እንዲረጋገጥ ይደረጋል፡፡ 9) የመንግስት የልማት ድርጅቶች የክልሉ ህዝብ ያሉበትን ተጨባጭ የልማት ችግሮች እየፈቱና ግልጽነትና ተጠያቂነት ባለው ስርዓት መመራት እንዳለባቸው እናምናለን፡፡ በመሆኑም የጥረት ኮርፖሬት እና የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም (አብቁተ) የተባሉት የልማት ድርጅቶች የክልሉ ህዝብ ሃብት እንደመሆናቸው መጠን የላቀ ልማት ማረጋገጥ በሚችሉበት አኳኋን መመራት ስላለባቸው ተጠሪነታቸውም ለክልሉ መንግስት እንዲሆን የፖለቲካ ውሳኔ ተወስኗል፡፡ አፈጻጸሙም ሕጉን ተከትሎ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ 10) በአሁኑ ሰዓት የተፈጠረውን ምቹ ሃገራዊና ክልላዊ ሁኔታ በመጠቀምና የዴሞክራሲ ምህዳሩን መስፋት እድል በማድረግ ሃገር ውሰጥ ከሚንቀሳቀሱም ሆነ ውጭ ሃገር በስደት ቆይተው ከተመለሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በሚያለያዩን ጉዳዮች ተከባብረን አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች አብረን ለመስራትና ዴሞክራሲን ለማስፋት ጽኑ ፍላጎት እንዳለንና በዚሁ መሰረት ለመራመድ ወስነናል፡፡ 11) በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል ያለው የድንበር ማካለል ጉዳይ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የሁለቱም ወገን አርሶ አደሮች የያዙትን የእርሻና የደን መሬት እንደያዙ እየተጠቀሙ እንዲቆዩ በሁለቱ ሃገራት መንግስታት መካከል ስምምነት ተፈርሞ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ በተለይ በመተማ ወረዳ ልዩ ስሙ ደለሎ በተባለው አካባቢ ታሪካዊ ዳራውንና ነባር የይዞታ መብታችንን ያላስጠበቀ፣ የሚመለከታቸውን አካላት ያላሳተፈና የጋራ አቋምም ያልተያዘበት ውሳኔ ተሰጥቶ እንደነበር አውቀናል፡፡ ይህ ውሳኔ ብአዴንና አመራሮቹ ለረጅም ጊዜ በህዝብ ዘንድ ባልተገባ መልኩ ሲታሙና ሲጠረጠሩ እንዲቆዩ አድርጓል፡፡ በመሆኑም ውሳኔው በፌዴራል መንግስት በኩል አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግበት እንጠይቃለን፡፡ ለጋራ የጸጥታ ማሰከበር ስራ ይጠቅማል የሚለውን ስምምነት ምክንያት በማድረግ በቋራ ወረዳ ልዩ ስሙ ነፍስ ገበያ በተባለው አካባቢ ለጊዜው ሰፍሮ የነበረው የሱዳን ወታደርም ይዞታ እያሰፋፋና ቋሚ ካምፕ እየገነባ ከያዘው ጊዚያዊ ይዞታ ሳይለቅ መቆየቱ ተገቢ እንዳልሆነ ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፡፡ የካመፑም መኖር የድንበሩን ጉዳይ የበለጠ እያወሳሰበውና የክልሉ አርሶ አደሮችም የእርሻ ስራቸውን በሰላም እንዳያከናውኑ እንቅፋት እየሆነ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የሱዳን ወታደር እስካሁን ድረስ ከያዘው ይዞታ ለቆ አለመውጣቱ ተገቢ ባለመሆኑ በፍጥነት ከይዞታችን ለቆ እንዲወጣና የፌዴራል መንግሥትም ይህንኑ እንዲያሰፈጽምልን እንጠይቃለን፡፡ ብአዴን በክልላችን የሚገኘው ይህ የኢትዮ ሱዳን የድንበር ጥያቄ የነዋሪዎችንና የአርሶ አደሮቻችንን ይዞታ መሰረት አድርጎ፣ ታሪካዊ ዳራውን ሳይለቅና የሃገርን ሉዓላዊ ጥቅም ባስከበረ መንገድ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድበት ጥረት ማድረግ እንደሚገባ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡ 12) ምሁራን የአማራ ክልልን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በሚደረገው ርብርብ የድርሻቸውን ለመወጣት እያሳዩ ያሉትን የጋለ ተሳትፎና ጥቁር መጋረጃውን የቀደደ ሞያዊ ግዴታን የመወጣት ታሪካዊ ዘመቻ ከልብ እናደንቃለን፡፡ በዚህም አጋጣሚ የአማራ ህዝብ በመላ፣ ወጣቶች፣ የሃይማኖት አባቶችና የድርጅታችን አባላት ከብአዴን ጎን ቆማችሁ ክልላችንና ሀገራችንን የመገንባት ጉዞ እንድትደግፉ ጥሪ እናቀርብላችኋለን፡፡ ለውጡን በመጠበቅ፣ በማጥለቅና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የእድገትና ትራንሰፎርሜሽን ዕቅዱን እናሳካለን!! የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ነሃሴ 19 ቀን 2010 ዓ.ም ባ/ዳር  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም