ቴክኖሎጂን በማላመድና በመቅዳት ወደ ተግባር በመለወጥ በኩል የተሰራው ሥራ አነስተኛ መሆኑ ተጠቆመ

3662

ባህር ዳር ግንቦት 9/2010 በአገሪቱ ቴክኖሎጂን በማላመድና በመቅዳት ወደ ተግባር በመለወጥ በኩል እየተሰራ ያለው ሥራ አነስተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ችግሩን ለመቅረፍና ወጥ የሆነ አሰራር መዘርጋት በሚቻልበት መንገድ ላይ ፖሊሲ አውጪዎችና አስፈጻሚ አካላት ጋር በባህር ዳር ከተማ እየመከሩ ነው።

የኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ግኝት ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ እዮቤል ገብረስላሴ እንደገለጹት እንደ ሀገር ቴክኖሎጂን አላምዶ ጥቅም ላይ የማዋል አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ ቢሆንም እየታየ ያለው ለውጥ አነስተኛ ነው።

ቴክኖሎጂ የሚያላምዱና አሻሽለው የሚሰሩ አካላት በማላመድ ጥቅም ላይ የሚያውሉት ቴክኖሊጂ ከሀገሪቱ የሥራ ባህል፣ በስፋት ከሚመረቱ ምርቶች፣ በሥራ ላይ ካሉ ፋብሪካዎች ጋር የሚጣጣሙ አለመሆናቸው ተፈላጊነታቸውን ዝቅተኛ እንዳደረገው ተናግረዋል።

“በዚህም በየጊዜው በተለያዩ ግለሰቦችና የትምህርት ተቋማት የተላመዱና ማሻሻያ ተደርጎባቸው የሚወጡ ቴክኖሎጂዎች ወደተግባር ሳይቀየሩ ውጤት አልባ ሆነው ይቀራሉ” ብለዋል።

አቶ እዩቤል እንዳሉት፣ ይህንን አሰራር ለማሻሻልና ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚሄድ ቴክኖሎጂን ለማላመድና አሻሽሎ ለመስራት ሁሉን አቀፍ ፖሊሲ ለማዘጋጀት እየተሰራ ነው።

እስካሁን ቴክኖሎጂን የሚያላምድና አሻሽሎ የሚሰራ ተቋምና ግለሰብ ሥራውን የሚያከናውነው በራሱ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ እንደነበር ጠቁመዋል።

ፖሊሲው በቀጣይ የሚሰሩ ሥራዎች ከሀገሪቱ የአሰራር ባህል ጋር የተዛመዱ ቴክኖሎጂዎችን ማላመድና ማሻሻል ላይ እንዲያተኩሩ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ አንድ የተሸሻለ ወይም የተላመደ ቴክኖሎጂ  በተላመደበት አካባቢ ብቻ ሳይሆን ሀግራዊ እውቅና ተሰጥቶት በእዚያው መሰረት ተደራሽነቱን ለማሳደግ የሚያስችል ነው።

የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው በበኩላቸው የግብርናውንም ሆነ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለማሳደግ ቀጥታ ቴክኖሎጂዎችን አስመጥቶ መጠቀም አዋጭ አለመሆኑን ገልፀዋል።

የሚላመዱም ሆነ የሚሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ለመለወጥ በጥናት ላይ የተመሰረተ ቴክኖሎጂ መጠቀም ተገቢና ተመራጭ መሆኑን ነው ያስረዱት።

በእስከዛሬ የቴከኖሎጂ ትግበራ ሂደት አዋጭነትን መሰረት ያደረገ አካሄድ እንዳልነበር ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ቴክኖሎጂን በማላመድና በማሻሻል የተጠቀሙ ሀገራትን ልምድ በመጠቀም አዲስ አሰራር ለመዘርጋት ጥናቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ለእዚህም ከደቡብ እስያ ሀገራት ልምድ በመውሰድ እየተሰራ መሆኑንና ለእዚህ የሚሆን የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚደረግ ነው ያስታወቁት።

ኢትዮጵያ በየዘርፉ ቴክኖሎጂን ከማላመድ ባለፈ መፍጠር የሚችል ባለሙያ እንዳላት የገለጹት ደግሞ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ መምህርና የዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ግንኙነት ዳይሬክተር ዶክተር ሲሳይ ገረመው ናቸው።

ቴክኖሎጂን ለማሻሻልና ለማላመድ የሚያስችሉ ጥሬ እቃዎች ከሰርቶ ማሳያ ያልዘለሉ መሆናቸው የተሸሻለውን ቴክኖሎጂ ወደ ተግባር ለመቀየር አስቸጋሪ እንዳደረገው ተናግረዋል።

መንግስት የማሻሻያና የማላመጃ ግብዓቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸው፣ የቴክኖሎጂ የትኩረት አቅጣጫዎች በአግባቡ ተቀምጠው የዘርፉ ምሁራን እንዲያተኩሩባቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባዮቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ካባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኢኒስቲትዩት ጋር በመተባበር ”ምልስ ቴክኖሎጂ” በሚል መሪ ሃሳብ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ የፌደራልና የክልል የዘርፉ ምሁራን ተሳታፊ ሆነዋል።