ቢሮው በጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ አደረገ

63

ደሴ ታህሳስ 17/2014 (ኢዜአ) -የአዲስ አበባ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ አሸባሪው ህወሀት በአማራና አፋር ክልሎች በከፈተው ጦርነት ለተጎዱ ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል፣ ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ አደረገ።

የቢሮው የሕግ ማስከበር ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ኮማንደር አህመድ መሀመድ ዛሬ በደሴ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን አስረክበዋል።

ኮማንደር አህመድ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት "እንደ ሃገር የገጠመንን ሁለንተናዊ ችግር ተጋግዘንና ተረዳድተን በጋራ እናልፋለን  '' ብለዋል።

"የገጠሙንን የዲፕሎማሲ፣ የኢኮኖሚና ሌሎች ሁለንተናዊ ችግሮቻችንን በጋራ ተጋግዘንና ተረዳድተን  እናልፋቸዋለን" ሲሉ አብራርተዋል።

"ቢሮው ለልማት ከሚሰበስበው ገቢ ጎን ለጎን በጦርነቱ የተጎዱ ወገኖችን በመደገፍ አገራዊ ግዴታውን ይወጣል" ሲሉም ተናግረዋል።

የቢሮው አመራሮችና ሰራተኞች በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ከ13 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የምግብ እህል፣ መመገቢያ ቁሳቁስና አልባሳት ድጋፍ  ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

ከድጋፉ ውስጥ 6 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው የምግብ እህል፣ ቁሳቁስና አልባሳት ለአማራ ክልል ተጎጂዎች፤ ቀሪው ደግሞ በአፋር ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የቀረበ መሆኑን አመልክተዋል።

ድጋፉ ሩዝ፣ ማካሮኒ፣ የምግብ ዘይት፣ እንዲሁም ፍራሽና ብርድ ልብስ ጨምሮ የተለያየ የመመገቢያ ቁሳቁስና የንጽህና መጠበቂያዎች ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

ቢሮው በቀጣይ የንግዱን ማህበረሰብ በማስተባበር በተደራጀ አግባብ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል ።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረመስቀል በበኩላቸው "የህወሀት ወራሪ ሃይል በደሴ ከተማ በቆየባቸው ቀናቶች ንጹሃንን ገድሏል፣ ደፍሯል፣ንብረት ዘርፏል እንዲሁም አውድሟል" ብለዋል።

ወራሪው በፈጸመው ግፍ ህብረተሰቡ ለከፋ ችግር መጋለጡን ጠቁመው "ይህን ወቅት ተጋግዞና ተደጋግፎ ለማለፍ ድጋፉ ወሳኝ ነው" ብለዋል።

ከመንግስትና መንግስታዊ ካልሆኑ ተቋማት የሚደረጉ ድጋፎች አቅመ ደካሞችና በጣም የተቸገሩ ወገኖችን ባስቀደመ አግባብ  በፍትሃዊነት እንደሚሰራጩ አስታውቀዋል ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ላደረገው ድጋፍ ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባው ተቋማትና ህብረተሰቡ እያደረጉ ያለውን ሰብአዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም