ትውልዱ እንደ አባቶቹ ሁሉ የሀገሩን ጥቅምና ክብር ሊያስቀድም ይገባል

60

ጅማ ታህሳስ 17/2014 (ኢዜአ) ትውልዱ ጀግነትና አልገዛም ባይነትን ከአባቶቹ በመውረስ የሀገሩን ጥቅምና ክብር ሊያስቀድም ይገባል ሲሉ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታየ ደንዳአ አስገነዘቡ።

የሰላም ሚኒስቴር የሶስተኛ ዙር የበጎ ፍቃድ ማህበራዊ አገልግሎት ሰልጣኞች ዛሬ በጅማ ዩኒቨርሲቲ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

በአቀባበል ስነስርአቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳአ "አኛ ኢትዮጵያውያን የጀግኖችና የአልገዛም ባይ ልጆች በመሆናችን አድለኞች ነን" ብለዋል።

"አባቶቻችን የጦር መሳርያ ሰርተው ጠላትን መክተዋል፤ አልባሳትና የቤት አቃዎቻቸውንም ሰርተው ተገልግለዋል፤ እኛም ከነሱ ተምረን ከባእድ ጥገኝነት ለመውጣት መስራት ይጠበቅብናል" ሲሉም ለበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች መልእክት አስተላልፈዋል።

"የአሁኑ ትውልዶች የአባቶቻችንን ታሪክ በመውረስ  የሀገራችን ጥቅምና ክብር ልናስቀድም ይገባል" ሲሉም አስገንዝበዋል።

የሰላምና የበጎ ፍቃድ አገልግሎት አምባሳደሮች የሆናችሁ ሰልጣኝ ወጣቶች ወንድማማችነትን፣ መተባበርና አንድነትን ልታጎለብቱ ይገባል" ሲሉ መክረዋል ።

በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ሀገራቸውን በመውደድ ለብሔራዊ አንድነት መስፈን የጎላ ሚናቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል ።

"ሰልጣኝ ወጣቶች ከተለያየ አካባቢ የመጡ በመሆናቸው የየአካባቢውን ባህልና ቋንቋ በመለማመድና በመለዋወጥ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራችሁን የበለጠ የተቃና ለማድረግ ልትተጉ ይገባል " ሲሉ አቶ ታየ ደንዳአ መልእክት አስተላልፈዋል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል አባ ፊጣ በበኩላቸው ለሰላምና ለበጎ ተግባር ስልጠና የመጡ እንግዶች የተሳካ ጊዜ አንዲሆንላቸው ተመኝተዋል።

ከዚህ በፊት በሁለት ዙር  የተሰጠው ስልጠና በተሳካ ሁኔታ የተጠናቀቀ መሆኑን ጠቁመው "ለሶስተኛ ዙር የገቡ ወጣቶችም ስልጠናቸውን ተከታትለው  የሰላምና የበጎነት ተምሳሌት ይሆናሉ" ሲሉ አመላክተዋል።

ለሶስተኛ ዙር ስልጠና አቀባበል ከተደረገላቸው 1 ሺህ 685 በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ውስጥ ከ500 በላይ ሴቶች ናቸው።

 ስልጠናው ለ45 ቀን እንደሚቆይ የወጣው መርሀ ግብር አመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም