ሩሲያ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የመልሶ ማቋቋም ተግባር ትደግፋለች

82

አዲስ አበባ ታህሳስ 17/2014(ኢዜአ) በኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ጉዳትና ውድመት መልሶ ለማቋቋም የሚከናወኑ ተግባራትን ሩሲያ ትደግፋለች ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴሬክሂን ተናገሩ።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉት አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴሬክሂን፤ አገራቸው የኢትዮጵያን መልሶ ማቋቋም እንቅስቃሴ እንደምትደግፍ ገልጸዋል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰውን ውድመትና በመሰረታዊነት የሚያስፈልጉ ነገሮችን ለማወቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

አምባሳደሩ በተለይም በመሰረተ ልማትና በተቋማት ላይ ከደረሰው ጉዳትና ውደመት አንጻር መልሶ ግንባታው ብዙ ጥረት ይፈልጋል ብለዋል።

"በዚህ ሂደት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ለማድረግ፣ የእኛ ድርሻ ምን መሆን እንዳለበትም እያሰብን ነው" ሲሉ ገልጸዋል።

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የአገራቸው መንግስት ድጋፍ ለማድረግ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተጠቃለለ የጉዳት ሪፖርት እስከሚወጣ ይጠብቃል።

በመቀጠልም የመልሶ ማቋቋም ስራው እንዴት መሆን እንዳለበትና የሩሲያ መንግስት ድርሻ ምን እንደሚሆን የመለየት ስራ ይሰራል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የገጠማትን ችግር እንድትሻገር ተጨባጭና ተግባራዊ እንስቃሴ እንደሚደረግም አክለዋል።

ይህም ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት በሚፈልገው መልኩ ሕይወቱን እንዲመራ ሩሲያ ድጋፏን ትቀጥላለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ መብቱ ተከብሮለት የመረጠውንና የፈለገውን ሕይወት እንዲሁም ዕጣ ፈንታውን የመወሰን የራሱ መብት እንዲከበርለት ሩሲያ ትታገላለች ነው ያሉት አምባሳደር ኤቭጌኒ ቴሬክሂን።

አምባሳደሩ በኢትዮጵያና ሩሲያ መካከል ያለው ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሠብዓዊ እንዲሁም የትምህርትና የጤና ዘርፍ ትብብር እያደገ መምጣቱንም አውስተዋል።

የአገራቱ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከምዕት ዓመት በላይ መሆኑን በመጥቀስም "ወደፊትም ሩሲያ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረገውን ጠልቃ ገብነት መቃወሟን ትቀጥላለች" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም