የደቡብ አፍሪካ ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 ዓመታቸው አረፉ

95

ታህሳስ 17 ቀን 2014 (ኢዜአ) በደቡብ አፍሪካ የአፓርታይድ ስርዓት እንዲወገድ የታገሉት የሰላም ኖቤል ተሸላሚ ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ90 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።

እ.አ.አ በ1931 የተወለዱት ሊቀጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ በ23 ዓመታቸው ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የመምህርነት ስራ ቢጀምሩም ከሶስት ዓመት በኋላ የስነ-መለኮት ትምህርት በመከታተል እ.አ.አ በ1960 ቅስና ተቀብለዋል።

ከዚያም ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ እንግሊዝ በማቅናት ለአራት ዓመታት የስነ-መለኮት ትምህርታቸውን ቀጥለው የማስተርስ ዲግሪ ተቀብለዋል።

ከዚያም ወደ አገራቸው ተመልሰው ስነ መለኮት ሲያስተምሩ ቆይተዋል።

በድጋሚ ወደ እንግሊዝ በማቅናትም በለንደን በሚገኝ የስነመለኮት ኢንስቲትዩት ረዳት ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል።

ከዚያም ወደ ደቡብ አፍሪካ ተመልሰው የሴይንት ሜሪ ካቴድራል የመጀመሪያው ጥቁር ዲን ሆነው ሰርተዋል።

እ.አ.አ በ1978 ደግሞ የደቡብ አፍሪካ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት የመጀመሪያው ጥቁር ዋና ጸሐፊ በመሆን መርተዋል።

ከብሪታኒያ፣ ጀርመንና አሜሪካ ለነበራቸው አገልግሎት የተለያየ የክብር ዶክትሬት ተቀብለዋል።

የዘር መድሎን በጽኑ ይታገሉ የነበሩት ሊቀጳጳስ ቱቱ እኩል የሲቪል መብት ለሁሉም፣ የደቡብ አፍሪካ የፓስፖርት ህግ እንዲታገድና ወጥነት ያለው ስርዓተ ትምህርት እንዲኖር ከፍተኛ ትግል በማድረግ ይታወቃሉ።

ለሰው ልጆች መብት መከበር በተለይም የዘር መድሎ ዋነኛ መለያው የሆነው የአፓርታይድ ስርዓት እንዲያበቃ ባደረጉት ትግልም የሰላም የኖቤል ሽልማትን ለማሸነፍ በቅተዋል።

ዛሬ ህልፈታቸው ለተሰማው ሊቀጳጳስ ህልፈተ ህይወት የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛን ጨምሮ በርካቶች የተሰማቸውን ሃዘን እየገለጹ እንደሚገኙ የተለያዩ ዘገባዎች አመልክተዋል።

ፕሬዝዳንት ራማፎዛ ለመጪው ትውልድ በአርአያነት የሚጠቀሱት ሊቃጳጳስ ዴዝሞንድ ቱቱ ህልፈተ ህይወት ለቤተክርስቲያኗ ምእመን ብቻ ሳይሆን ለደቡብ አፍሪካውያን ትልቅ ሃዘን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም