አሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በአጣየና መሃል ሜዳ ማረሚያ ቤቶች ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ ሃብት ዘርፈዋል

97

ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአሸባሪዎቹ ህወሃትና ሸኔ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አጣየና መሃል ሜዳ ማረሚያ ቤቶች ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት መዘረፉን የዞኑ ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ገለጸ።

ማረሚያ ቤቶችን ወደ ሥራ ለማስገባት የሚረዳ አንድ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የቁሳቁስ ድጋፍ በተደረገበት ወቅት የዞኑ ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር ቀፀላ ደበበ እንዳሉት፤  አሸባሪ ቡድኖቹ ማረሚያ ቤቶችን በማውደምና በመዝረፍ ጉዳት አድርሰዋል።

ውድመት ካደረሱበት ንብረት በተጨማሪ ከ16 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሃብት መዘረፉን ገልጸዋል።

የሽብር ቡድኖቹን ዕኩይ ሴራ በማክሸፍ ተቋማቶቹን ሥራ ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሃላፊው፤ የማረሚያ ቤቶቹን ችግር በጊዜያዊነት በማቃለል ሥራ ለማስጀመር ኮምፒውተር፣ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስ፣ የማብሰያና  ሌሎችን  እቃዎች በድጋፍ  መገኘቱን ተናግረዋል።

እንደ ኮማንደር ቀፀላ ገለጻ፤  ድጋፉ የተሰጠው ከዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽህፈት ቤት ከዓለም ከተማ ማረሚያ ቤትና ሌሎች ተቋማት ጋር በመተባበር ነው።

የአጣየ ማረሚያ ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ቁምላቸው ጌጤ በበኩላቸው፤ በሽብር ቡድኖቹ የማረሚያ ቤቱ የውስጥ ቁሳቁስ ተዘርፏል፤ የቀረውም ለብልሽት ተዳርጓል ብለዋል።

የህግ ታራሚዎች መገልገያ የነበሩ መኝታዎች፣ የምግብ ማብሰያ ቁሶች፣ የማሰልጠኛና የማስተማሪያ መሳሪዎች፣ መድሃኒቶችና ሌሎች 10 ሚሊዮን ብር ግምት ያላቸው ንብረቶችም መዘረፋቸውን ነው ያመለከቱት።

በአሁኑ ወቅት ማረሚያ ቤቱን ቀድሞ ወደሚሰጠው አገልግሎት ለማስገባት የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመው፤ የተደረገው ድጋፍ ማረሚያ ቤቱን ሥራ ለማስጀመር መነሻ ይሆናል ብለዋል።

በሽብር ቡድኖቹ ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የስፌት መኪና፣ የሽመና መሳሪዎች፣ ኮፒውተሮችና ሌሎች የማረሚያ ቤቱ ሃብቶች ተዘርፈዋል ያሉት ደግሞ የመሀል ሜዳ ማረሚያ ቤት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኮማንደር በጋሻው ሳህለ ናቸው።

ኮማንደሩ ለተደረገው  ድጋፍ አመስግነው፤ ማረሚያ ቤቱ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጥ በቀጣይም ሌሎች ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል። 

_ አካባቢህን ጠብቅ፣

_ ወደ ግንባር ዝመት፣

_ መከላከያን ደግፍ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም