በኢትዮጵያ ሠላምና ብሔራዊ መግባባት እንዲሰፍን ምሁራን ህብረተሰቡን የማንቃት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል

75

ሀዋሳ፤ ታህሳስ 16/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ ሠላምና ብሔራዊ መግባባት የሰፈነባት ጠንካራ ሀገር እንድትሆን ምሁራን ገንቢ ሀሳብ የማፍለቅና ህብረተሰቡን የማንቃት ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደአ ተናገሩ።

የሰላም ሚኒስቴር ከሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በውጭ ጣልቃ ገብነት፣ ብሄራዊ መግባባትና በኢትዮጵያ የሠላም ፖሊሲ ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ በሀዋሳ ከተማ አካሂዷል።

ሚኒስትር ዴኤታው በመድረኩ  እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ቀደምት የሥልጣኔ ምንጭ ከመሆን ባለፈ በተፈጥሮ ሀብት የታደለች ሀገር ናት።

ይህንን ሁለንተናዊ ፀጋ በማቀናጀትና በመደመር ወደ ሚፈልገው ብልፅግና ማማ ለመሻገር በብሔራዊ ደረጃ መግባባት በመፍጠር በየደረጃው የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ምሁራን በሠላምና ሀገር ግንባታ ላይ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በተለይ ገንቢ ሀሳቦችን በማፍለቅ ህብረተሰቡን የማንቃት ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ምክንያታዊ ትውልድ እንዲፈጠር ብሎም የተሳሳቱ ትርክቶችን በአንክሮ በመመልከትና በማጥራት በሀገር ደረጃ የጋራ መግባባት እንዲፈጠር በየደረጃው ሊሰሩ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በኢትዮጵያ ላይ ለመፈጸም እየተሞከረ ያለው የውጭ  ጫናን ለመመከት ምሁራን ነባራዊ ሁኔታዎችን የመተንተንና ለማህበረሰቡ የማሳወቅ ሚና እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

ኢትዮጵያ ወዳለመችው የብልፅግና ማማ ከፍ ለማለት ሠላሟን አስተማማኝና ዘላቂ ማድረግ ያስፈልጋል ያሉት አቶ ታዬ ፤ ሚኒስቴሩ  ይህንን ጉዳይ በፖሊሲ ለመምራት የሠላም ፖሊሲ የመቅረፅ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር አያኖ በራሶ በበኩላቸው ፤ብሔራዊ መግባባት የሚጀምረው ከቤትና ከሚኖሩበት ማህበረሰብ በመሆኑ የሀገር ውስጥ ዲፕሎማሲ ከውጪ ዲፕሎማሲው ያልተናነሰ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ለማህበረሰባዊ ተግባቦት ሥራዎችም እንዲሁ።

ለዚህ እውን መሆን ዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ዲፕሎማሲ ማዕከል በማቋቋም ምሁራን ማህበረሰቡን የሚያስገነዝቡበትና ህዝቡን በጋራ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የሚያነቁበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

ምሁራን ኢትዮጵያ በአሁኑ  ወቅት ያጋጠማትን የውጭ ጣልቃ ገብነትና ጫና ከመመከት በተጓዳኝ  ለሀገር ልማትና ግንባታ የሚጠበቅብንን የቤት ሥራ መስራት ይገባናል ያሉት ደግሞ በመድረኩ  የመወያያ ፅሁፍ ያቀረቡት በዩኒቨርሲቲው የፖሊሲና ልማት ፣ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒዩኒኬሽን መምህርና ተመራማሪ ዶክተር መልሰው ደጀኔ ናቸው ።

ዶክተር መልሰው እንዳሉት፤ ምሁራን ለሀገር ጥቅምና ብልጽግና ጉዞ ስኬታማነት ቅድሚያ በመስጠት ለማህበረሰባዊ ለውጥ የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን መምህር ተስፋዬ አለማየሁ፤ ከዚህ በፊት ምሁራን በነበረባቸው ፖለቲካዊ ፍረጃና አግላይ ሥርዓት ምክንያት በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ባይተዋር ሆነው ቆይተዋል ነው ያሉት።

ይህ ሁኔታ አሁን ላይ እየተለወጠ መምጣቱን ጠቅሰው፤ በተለይ የዚህ ዓይነት መድረክ መዘጋጀቱ ምሁራን የሚጠበቅብንን ሚና እንድንወጣ አጋዥ ይሆናል ብለዋል።

አሁን ላይ የውጭ ጫናን በመመከት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ህዝባዊ አንድነትን በማጠናከር ፣በብልሀትና በጥንቃቄ መምራት እንደሚያስፈልግ ያመለከቱት ምሁሩ ፤" እኛም መንግስታችንን በህብረት መደገፍ ይጠበቅብናል" ሲሉ አመልክተዋል።

በምክክር መድረኩ  ከሰላም ሚኒስቴር፣ ከሀገሪቱ 12 የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የተውጣጡ የሥራ ሃላፊዎች ፣ ምሁራንና ተማሪዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም