"ወጣትነቴ ለሃገሬ " በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው የወጣቶች ንቅናቄ ጥሩ ውጤት እያስመዘገበ ነው

62

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከቀያቸው በግፍ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ''ወጣትነቴ ለሃገሬ'' በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረው የወጣቶች ንቅናቄ ጥሩ ውጤት እየታየበት መሆኑን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለጸ።

ወራሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች በርካታ ንጹሀንን ጨፍጥፏል፤ መሰረተ ልማቶችን አውድሟል፤ መኖሪያ ቤቶችን ጭምር አቃጥሏል፤ ዜጎችንም በግፍ ከቀያቸው አፈናቅሏል።

ይህንንም ተከትሎ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከ15 ቀን በፊት ከቀያቸው በግፍ የተፈናቀሉ ንጹሃን ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በድሬደዋ ከተማ ሃብት የማሰባሰብ ንቅናቄ መርሃግብር መጀመሩ ይታወሳል።

ከቀያቸው በግፍ የተፈናቀሉና ቤታቸው በአሸባሪው ቡድን የተቃጠለባቸውን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም በወጣቶች በተደረገው ንቅናቄ ጥሩ ምላሽ መታየቱን የወጣቶች ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሙና አህመድ ገልጸዋል።

ንቅናቄው ከታህሳስ 1 ጀምሮ እስከ የካቲት 30 ለሦስት ወራት የሚቆይ ሲሆን፤ በሁሉም ክልሎች ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።

''ወጣትነቴ ለሃገሬ'' በሚል መሪ ቃል ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ የወጣቶች ሊግ፣ የወጣቶች ማህበር እና የወጣቶች ፌዴሬሽን በጋራ እንደሚሰሩም ጠቁመዋል።

ወጣቱ የቤት ቆርቆሮ፣ ምስማር፣ ሲሚንቶና የመሳሰሉ የቤት መሥሪያ ቁሳቁሶችን እያሰባሰበ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በታህሳስ ወር ሃብት የማሰባሰብና ግንዛቤ የመፍጠር ሥራ እየተከናወነ ሲሆን፤ በቀሩት ሁለት ወራት ደግሞ ሥፍራው ድረስ በመሄድ በጉልበት የማገዙ ሥራ እንደሚቀጥል ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል።

ዜጎች በፊት ይኖሩበት ከነበረው መኖሪያ ቤት በተሻለ መንገድ በመሥራት የደረሰባቸውን ጉዳት እንዲረሱ የማድረግ ሥራ ለማከናወን ወጣቶቹ ያላቸው ተነሳሽነት ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ሁሉም ስሜቱን ሊጋራው ይገባል ብለዋል።

ሁሉም ወጣት በዘመቻው በመሳተፍ አጋርነቱን እንዲያሳይና ታሪካዊ አሻራውን እንዲያሳርፍም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም