በጋምቤላ ክልል በ5 ወራት ውስጥ ከ427 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ተሰበሰበ

136

ጋምቤላ ፤ታኅሣሥ 16/2014(ኢዜአ) በጋምቤላ ክልል በ5 ወራት ውስጥ ከ427 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ።

በክልሉ የገቢ አማራጮችን በማስፋት የሚሰበሰበውን ገቢ ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም የጋምቤላ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታውቋል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ኤልያስ ለኢዜአ እንዳሉት፤በኢኮኖሚው ዘርፍ በሀገሪቱ ላይ  እየተደረገ ያለውን ጫና ለመቋቋም የገቢ አቅምን ማሳደግ  ያስፈልጋል፣ "በዚህም ክልሉ የድርሻውን ለመወጣት ያሉትን የገቢ አማራጮች በመጠቀም ለመሰብሰብ በትኩረት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

በክልሉ ባለፉት አምስት ወራት ገቢን ለማሳደግ በተከናወኑት ሥራዎች የአምስት ወረዳዎችን ሪፖርት ሳይጨምር ከተለያዩ የገቢ አርዕስቶች ከ427 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን አመልክተዋል።

ገቢው የእቅዱን 87 በመቶ ሲሸፍን፤  ካለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር ደግሞ በ45 ሚሊዮን ብር ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል።

ገቢው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት የተሻለ መሰብሰብ የተቻለው ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች የሥራ ግብርና ሌሎች የገቢ ምንጮች አሰባሰብ ላይ በነበሩ ክፍተቶች ላይ ማስተካከያ  በመደረጉ ነው ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ ለመሰብሰብ የታቀደውን ግብ ለማሳካት በትኩረት እንደሚሰራም ወይዘሮ ገነት ገልጸዋል።

በተለይም እንደ ሀገር የኢኮኖሚ ተፅዕኖ ለማሳረፍ የሚደረገውን ጫና ለመቋቋም እየተደረገ ላለው ጥረት ስኬታማነት ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ የዜግነት ግዴታውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ከጋምቤላ ከተማ ነጋዴዎች መካከል አቶ ጌትነት ይበይን በሰጡት አስተያየት፤ የመንገድ፣ የትምህርት ፣የጤናና ሌሎች የመሰረተ ልማት አውታሮች ማሟላት የሚቻለው ዜጎች ያለባቸውን ግብር በአግባቡ መክፈል ሲችሉ  መሆኑን ተናግረዋል።

ያለባቸውን ግብር ያለማንም ጎትጓችነት በወቅቱ መክፈላቸውን የጠቆሙት ግብር ከፋዩ፤ "በተለይም አሁን ላይ በሀገሪቱ የኢኮኖሚ ጫና ለመፍጠር የሚደረገውን ተጽዕኖ ለመቋቋም ሁሉም ያለበትን ግብር በወቅቱ ሊከፍል ይገባል" ብለዋል።

ሌላው ግብር ከፋይ አቶ ደምስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ የሚጠበቅባቸውን ግብር በወቅቱ ገቢ ማድረጋቸውን ገልጸው "ልጆቻችን ትምህርታቸውን መከታተል የሚችሉትም ሆነ ሌሎች የልማት ጥያቄዎች መንግስት መመለስ የሚችለው ዜጎች ያለባቸውን ግብር በአግባቡ መክፈል ሲችሉ ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም