“የህወሃት ጭካኔ ዘግናኝ ቢሆንም አንድ አድርጎናል”

108

አሶሳ ፣ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) “የህወሃት ጭካኔ ዘግናኝ ቢሆንም አንድ አድርጎናል” 

ጥቅምት 24 / 2013 ዓመተ ምህረት ሽብርተኛው ህወሃት ኢትዮጵያን የማፍረስ ህልሙን ለማሳካት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመው ጥቃት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ሁሌም ሲታወስ የሚኖር ነው፡፡

የሽብር ቡድኑን የተሰጠውን የጽሞና ጊዜ በመርገጥ በአጎራባች ክልሎች ወረራ መቀጠሉን ተከትሎ መንግስት ሀገርን ለማስቀጠል  በዘመቻ ለህብረ ብሄራዊ አንድነት እርምጃ እንዲወስድ አድርጎታል ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብም ጥሪውን ተቀብሎ ፈጣን ተግባራዊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ ህብረተሰቡ በተለይም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያለው ክብርና ድጋፍ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ከፍ እንዲል አድርጎታል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ህዝብም ሀገርን ለማፍረስ የሚደረግ የውስጥ እና የውጪ ሃይሎችን እንቅስቃሴ በተደጋጋሚ በአደባባይ ወጥቶ አውግዟል፡፡

ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በፈቃዳቸው ተቀላቅለዋል፡፡ ነዋሪው ደም እየለገሰ ስንቅ ከማዘጋጀት ጀምሮ በጥሬ ገንዘብ ያለውን ሳይሰስት በመስጠት ለመከላከያ ሰራዊቱ አለኝታነቱን በግልጽ አስመስክሯል፡፡

“ሽብርተኛው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲነሳ በሰሜን እዝ የመከላከያ ሠራዊታችን ላይ የፈጸመውን ግፍ መቼም አንዘነጋውም፡፡ የህወሃት ጭካኔ ዘግናኝ እና የማይረሳ ቢሆንም እንደ ሃገር ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድ አድርጎናል፡፡”

የሚሉት በግንባር ለሚፋለመው ሰራዊት ስንቅ ሲያዘጋጁ ያገኘናቸው የአሶሳ ነዋሪ ወይዘሮ እጸገነት ተስፋዬ ናቸው ፡፡

"በሠራዊታችን እንኮራለን፤ መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው መከላከያ  የኋላ ደጀን ለመሆን የምናከናውነው ነገር ሁሉ በራሳችን ተነሳሽነት ነው፤ ከጸጥታ ሃይሉ ጋር በመቀናጀት በቀን እና በምሽት አካባቢያችንን ከህወሀት ርዝራዦች ተደራጅተን እየጠበቅን ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ሀገርን ማስተዳደር የሚቻለው መጀመሪያ ሀገር ሲኖር ነው፤ ብሎ ወደ ግንባር የሚዘምት መሪ አግኝተናል የሚሉት ነዋሪዋ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ሠራዊቱን በግንባር ተሰልፈው በመምራት ላሳዩት ቆራጥነት ለተሞላበት ተግባር ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል፡፡

"የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተግባር የአባቶቻችንን የድል ታሪክ የደገመ ነው" ሲሉም ጠቅሰዋል፡፡

"ሽብርተኛው ህወሃት ህጻናት ልጆችን ጭምር የጦርነት መጠቀሚያ አድርጓል" ያሉት ደግሞ ወይዘሮ አወዲፍ መሃመድ ናቸው። 

"ወልዶ መሳም እና ማሳደግ የሚቻለው ሀገር ሲኖረን ነው" ያሉት ነዋሪዋ፤ ይህን መሠረት በማድረግ ደማቸውን ለሀገር መከላከያ ሠራዊት የለገሱ ሲሆን ወርሃዊ ደመወዛቸውንም  በመስጠት ድጋፍ ማድረጋቸውን አንስተዋል፡፡

"መከላከያ ሠራዊቱ በሽብር ቡድኑ ላይ ያስመዘገበው ድል እንዲቀጥል ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታችንን በማጠናከር ከሠራዊታችን ጎን መቆም ይጠበቅብናል" ሲሉም ወይዘሮ አወዲፍ ተናግረዋል፡፡

"የዘማች ቤተሰቦችንና የአርሶ አደሩን የደረሱ  ሰብሎች በመሰብሰብ ለሀገር ህልውና አለኝታነታችንን ለማረጋገጥ ያደረግነውን ጥረት የአንዳንድ የምእራባውያን መገናኛ ብዙሃን አዛብተው መዘገባቸው አስቆጭቶኛል " ያለችው ደግሞ የ10ኛ ክፍል ተማሪዋ ሊዲያ ጽጉ ናት፡፡

"የትኛውም አይነት የሃሰት ዘገባ ሠራዊታችንን ከመደገፍ አይከለክለንም" ያለችው ተማሪ ሊዲያ፤ "አላወቁትም እንጂ ሐሰተኛ ዘገባውቸው እስከ ግንባር እንድንዘምት የበለጠ አነሳስቶናል" ብላለች፡፡

"ሰብል በመሰብሰብ፣ ደም በመለገስ፣ ስንቅ በማዘጋጀት እና ለተፈናቃዮች ድጋፍ በማሰባሰብ ለሠራዊቱ ቤተሰብ ያደርግነው ድጋፍ በቂ አደለም" ያለችው ተማሪ ሊዲያ፤ "ከመከላከያ ጎን ቆመን እስከ ህይወት መስዋዕትነት ከመክፈል የሚያግደን ነገር የለም" ስትል አቋሟን ገልጻለች፡፡

አቶ ዋቅጋሪ ዋቆያ በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት ከመሸገበት ትግራይ ፤ አሸባሪው ሸኔ ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ ካልጠፉ ኢትዮጵያ ወደ ቀደመ ሠላሟ ትመለሳለች ብለው እንደማያምኑ ገልጸዋል፡፡

መከላከያ ሠራዊቱ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስት በሽብር ቡድኑ ላይ እየወሰዱ የሚገኘውን  እርምጃ አቅማቸው በፈቀደ ሁሉ እንደሚደግፉና የሽብር ቡድኑ እስኪወገድም ድጋፋቸው እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

"ኢትዮጵያ በታሪኳ በርካታ ጦርነቶችን በድል አድራጊነት አልፋለች" ያሉት ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ከበደ ናቸው፡፡ የሽብርተኛው ህወሃትን ያህል ዜጎችን አዋርዶ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሞከረ  ሃይል እንደማያውቁ ጠቅሰው ፤የሰማንያ ዓመት አዛውንት ላይ ጭምር ያደረሰው ዘግናኝ አስገድዶ የመድፈር ወንጀልን በቁጭት አስታውሰዋል፡፡

ሰይጣናዊ ድርጊት ሲፈጽም ለኖረው አሸባሪው የህወሃት ቡድን በጭካኔው ልክ ለመናገርና ለመግለጽ ቃላት እንደሚያጥራቸው ገልጸዋል፡፡

"ኢትዮጵያ በውጪ ሃይሎች ተገዝታ አታውቅም" ያሉት ወይዘሮ ሁሉአገርሽ ፤ከህወሃት ጀርባ ያሉ ሃያላን ሀገራት ምኞት እንዳይሳካ መከላከያ ሠራዊታችን የህይወት መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ ሽብርተኞቹን ድባቅ እየመታ መሆኑ እንደሚያኮራቸው ተናግረዋል፡፡

በግላቸው ለመከላከያ ሠራዊት ደመወዛቸውን መስጠታቸውን ደም መለገሳቸውን ገልጸው ይህንንም አጠናክሬ በመቀጠል መከላከያን መደገፍ የውዴታ ግዴታዬ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ለ27 ዓመት ሀገር የዘረፈው ሽብርተኛው ህወሃት አሁንም በዚሁ ድርጊቱ ለመቀጠል ኢትዮጵያን ማተራመሱ እንደሚያስገርማቸው የተናገሩት ደግሞ በምሽት አካባቢያቸውን ሲጠብቁ ያገኘናቸው አቶ ቤኩማ ሹራ ናቸው።

"እኛ ሌላ ሀገር የለንም የምንሞተው ለኢትዮጵያ ነው" ያሉት ነዋሪው፤ "ፍጻሜው የተቃረበውን ሽብርተኛውን ህወሃት ለማሶገድ የበኩላችንን እንወጣለን" ሲሉ ገልጸዋል፡፡

"ይህን ለማሳካት ዋነኛው መንገድ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በሙሉ አቅም መደገፍ ነው" ያሉት ነዋሪው " ተደራጅተን ከሰራዊቱ ጎን በመሆን አካባቢያችንን ከሰርጎ ገቦች መጠበቅ የእለት ተእለት ተግባራችን አድርገናል" ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአሶሳ ከተማ ነዋሪ ከሆኑ የትግራይ ተወላጆች መካከል አቶ ሙሉአለም አበበ ከአንድ መንደር የተሰበሰቡ ጥቂት የሽብርተኛው ህወሃት አመራሮች አገር በመዝረፍ እና በማራቆት በትግራይ ህዝብ ስም ሲነግዱ መቆየታቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሰሜን እዝ ላይ በፈጸሙት ጥቃት የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግስትን ወደ ማይፈልጉት ጦርነት እንዳስገቡ ነዋሪው አስረድተዋል፡፡

ህወሃት ለኢትዮጵያ ህዝብ ደንታ እንደሌለው በተለይም በቅርቡ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ  ያደረሰው ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ ዘረፋ፤ የሃይማኖት ተቋማት ውድመት ዋነኛ ማሳያዎች እንደሆኑ ይጠቅሳሉ፡፡

"ትግራይ ያለ ኢትዮጵያ ዋጋ የላትም" ያሉት ነዋሪው የሽብር ቡድኑ ሀገርን የማፍረስ እቅዱ ሳይሳካ መቅረቱን ተናግረዋል፡፡ ህወሀት ህዝብን በማደናገር ስልጣኑን ለማስቀጠል ትግራይን ከኢትዮጵያ እገነጥላለሁ በሚለው ምኞት ሆኖ በቀረው ህልሙ መቀጠሉን አቶ ሙሉአለም ጠቅሰዋል፡፡

ሽብርተኛውን ህወሃት ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ እንዲወገድ የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድሞቹ ጎን በመቆም በቃህ ሊለው የሚገባበት ጊዜ አሁን እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ፍጻሜን ለማፋጠን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ ከተጀመረ ወራት ተቆጥረዋል፡፡

የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በሰጡት አስተያየት ህብረተሰቡ ለሠራዊቱ የሚያደርገው ድጋፍ ኮሚቴው ከጠበቀው በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

"በሁለት ተከታታይ ዙሮች ብቻ 30 ሚሊዮን የሚጠጋ ብር  ተሰብስቦ ለሠራዊቱ ገቢ ተደርጓል፣ የደረቅ ስንቅ፣ የደም ልገሳ፣ የእርድ እንስሳት እና ሌሎችም የአይነት ድጋፎችም ተካሂደዋል ብለዋል።

"ኮሚቴው ካለፈው ሳምንት ጀምሮ እያካሄደ በሚገኘው ሶስተኛ የገቢ ማሰባሰብ መርሀ ግብር  17 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ ከ65 በመቶ በላይ እቅዱን ማሳካት ችሏል" ብለዋል፡፡

ህብረተሰቡ ለመከላከያ ሠራዊት የሚያደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ኮሚቴው አቅሙን አሟጦ የህዝብ ንቅናቄ ስራዎችን በስፋት እያከናወነ መሆኑን አቶ ኢሳቅ አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም