ከጦርነቱ ወዲህ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለማቃለል የተፈጥሮ ሀብትና የሰው ሃይልን በቅንጅት መጠቀም ይገባል-ምሑራን

100

ጂንካ ፣ ታህሳስ 16/2014(ኢዜአ) ከጦርነቱ ማግስት ሊፈጠሩ የሚችሉ የተለያዩ ችግሮችን ለማቃለል የመሬት፣ የውሃና የሰው ሃይልን በተቀናጀ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

የዩኒቨርሲቲው ምሁራን ለኢዜአ እንዳስታወቁት ኢትዮጵያ በአሸባሪ ህወሓትና በአንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ሳቢያ እየገጠማት ያለውን የኢኮኖሚ ችግር ለመቋቋም ጠንካራና የማይበገር ኢኮኖሚ መገንባት አለባት።

የዩኒቨርሲቲው መምህርና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪ ዶክተር ኃይለጊዮርጊስ ቢራሞ "ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ የተጎዳውን ኢኮኖሚና ይህንኑ ተከትሎ ምዕራባውያን ሊጥሉባት የሚሹትን ማዕቀብ ለመቋቋም በጋራ መነሳት ይገባናል" ብለዋል።

አንዳንድ ምዕራባውያን አገሮች ጠንካራ መንግሥት ለመመስረት በሚጥሩ  አዳጊ አገሮች ላይ ማዕቀብ በመጣል ኢኮኖሚያቸው እንዳያንሰራራና ለእነሱ ተገዢ እንዲሆኑ የማድረግ ጽኑ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረው ይህንንም ኢትዮጵያን በመሰሉ አገሮች ላይ በመተግበር ጉዳት ያደርሳሉ ነው ያሉት።

"በተለይ አሜሪካ በአሁኑ ወቅት በአገራችን የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ የምትገባው የበላይነቷን ለማስጠበቅ ነው" ሲሉም ዶክተር ኃይለጊዮርጊስ ተናግረዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በኢኮኖሚም፣ በፖለቲካውም ሆነ በማህበራዊ ዘርፎች ቀጣናዊ ትስስር መፍጠር እንደሚፈልጉ ምእራባውያን ስለሚያውቁ በቀይ ባህር ካላቸው ሚና ጋር በማያያዝ ጫና ለማሳደር እየሞከሩ መሆናቸውን አስረድው በዚህም በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫና እየከፋ መምጣቱን አመልክተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምጣኔ ሀብት መምህር ጀማል መካሻ  በበኩላቸው አሜሪካ  ለአፍሪካ አገሮች ሰጠሁ የምትለው የኢኮኖሚ ዕድል ከጠቀሜታው ይልቅ፤ማስፈራሪያ  ስታደርገው  እንደሚስተዋል ገልጸዋል።

አፍሪካውያን ከአሜሪካና የምዕራባውያን ጫና የሚቋቋም ጠንካራ ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚያስፈልጋቸውም አመልክተዋል።

"በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በአሸባሪው ህወሓት ቡድን የወደመውን ሀብትና ንብረት ለመተካትና ጦርነቱን ተከትለው የሚመጡ  ቀውሶችን ለመከላከል ስልቶችን መቀየስ  ያስፈልጋል" ብለዋል ምሁሩ።

ከጦርነቱ ማግስት ሊፈጠሩ የሚችሉትን የኑሮ ውድነት፣ የአቅርቦት እጥረትና የሥራ አጥነት ችግሮችን ለማቃለል የመሬት፣ የውሃና የሰው ሃይልን በተቀናጀ መልኩ ጥቅም ላይ ማዋል እንደሚገባ መምህር ጀማል አስገንዝበዋል።

"በጦርነቱ ምክንያት ከተፈጠሩት ማህበራዊ፣ ሥነ ልቡናዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች ለመውጣት ጥምረት መፍጠር ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ናቸው።

"በተለይ ዩኒቨርሲቲዎች በጦርነቱ ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች በተናጠል ከሚያደርጉት ድጋፍ በተጨማሪ በጦርነቱ ወቅትም ሆነ ከጦርነቱ ማግስት የሚፈጠሩ ቀውሶችን ለመከላከል ጥምረት በመመስረት ድጋፍ ማድረግ ይገባናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም